|
በአማራ ክልል ከ5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች ፈቃድ ተሰጠ |
| ባህርዳር ጥቅምት 9/1999/ ዋኢማ/ በአማራ ክልል ባለፉት ሶስት ወራት 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ላቀረቧቸው 160 ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ኤጀንሲ አስታወቀ። በኤጀንሲው የጥናትና ማስፋፈፊያ መምሪያ ኃላፊ አቶ አሰፋ ወርቄ ትናንት ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ባለፉት ሦስት ወራት በኤጀንሲውና በፌደራል የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኩል 160 ፕሮጀክቶች በክልሉ ልማት ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ፈቃድ አግኝተዋል። ፕሮጀክቶቹ ከውጪ በመጡ ባለሀብቶች፣ በውጪና በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ሽርክና እንዲሁም ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚካሄዱ መሆናቸውን አቶ አሰፋ አስታውቀዋል። ባለሀብቶቹ በግብርና፣በኢንዱስትሪ፣በኮንስትራክሽን ፣በማህበራዊ አገልግሎት፣በሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም በልዩ ልዩ የንግድ ሥራ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ኃላፊው አስረድተዋል። የሩብ ዓመቱ የክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በካፒታል የ145 በመቶ እንዲሁም በፕሮጀክቶች ብዛት ከ62 በመቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱን አብራርተዋል። ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ መጨመር በክልሉ ውስጥ በሚገኙት በጎንደር፣ደሴና ደብረብርሃን ከተሞች የኢንቨስትመንት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን በመክፈት ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት መቻሉና ቀደም ሲል በመስሪያ ቦታ አሰጣጥ ይከሰቱ የነበሩ ችግሮች መወገዳቸው አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም ከባለሐብቶችና ከመንግሥት አካላት የተውጣጣ አንድ ቡድን በአዲስ አበባ ከተማ ተቋቁሞ ከፍተኛ የቅስቀሳ ሥራ ማካሄዱና በባህርዳር ከተማም አንድ የኢንቨስትመንት አገናኝ ቢሮ መከፈቱና የተለያዩ የማስታወቂያ ሥራዎች መከናወናቸው በክልሉ የባለሐብቶች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን ገልፀዋል። ፈቃድ የተሰጣቸው ፕሮጀክቶች ግንባታ ለመጀመር የሚያስችላቸውን ዝግጅት እያካሄዱ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አሰፋ፤የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ማምረት ተግባር ሲሸጋገሩ ከ29 ሺ 720 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ አስረድተዋል። በክልሉ እስካሁን ከ18 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 1 ሺ 338 ፕሮጀክቶች ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን፤326 ያህሉ ሙሉ በሙሉ ወደ ማምረት ተግባር በመሸጋገራቸው 48 ሺ 456 የሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ማግኘታቸውን ከኃላፊው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል። |
|
|
|
|