አንድ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ከፍተኛ የአመራር አባል እጃቸውን ለኢትዮጵያ ሰጡ

ጅጅጋ ጥቅምት 9/1999 /ዋኢማ/ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና በግንባሩ የኤርትራና የኬንያ አስተባባሪ የነበሩት አንድ ከፍተኛ አመራር አባል እጃቸውን ለኢትዮጵያ መንግስት መስጠታቸውን የሶማሊ ክልል የፀጥታና ፍትህ ማስተባበሪያ ጠቅላይ ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ የፀጥታና ፍትህ ማስተባበሪያ ጠቅላይ ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዲ መሀመድ እንደገለፁት ሰሞኑን እጃቸው የሰጡት አቶ አደን ዩሱፍ ታጊ የግንባሩ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራር ሲሰጡ የቆዩ ናቸው።

ግለሰቡ ሰላማዊ መንገዱን በመምረጥ እንደማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት በአገራቸው ሰላማዊና ፖለቲካዊ ትግል ለማካሄድ ወደ አገርቤት ሲገቡ በሺዎች የሚቆጠሩ የዋርዴር ከተማ ህዝብ ፤የመከላከያ አመራሮች ፤ የክልሉ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች ፤ የጎሳ መሪዎች የሞቀ አቀባበል እንዳደረጉላቸው ገልፀዋል።

የፌደራልና የክልሉ መንግስት በተሳሳተ ዓላማ ጸረ አትዮጵያና ጸረ የክልላቸው ህዝብ ሆነው የቆዩት የግንባሩ አመራሮችና አባላት ሰላማዊ ኑሮ መርጠው ከተመለሱ የበደሉትን ህዝብ እንዲክሱና በአካባቢው የልማት ስራ እንዲሳተፉ ሁኔታዎች እየተመቻቸላቸው እንደሚገኝ አቶ አብዲ መሃመድ ገልጸዋል ።

አቶ አደን ዩሱፍ ታጊ እንደ አውሮፖውያን አቆጣጠር ከ1994 እሰከ 1998 በግንባሩ የዋርዴር ዞን የሰራዊቱ ክንፍ አዛዥ ከ2000 እስከ 2001 በግንባሩ የኬንያና የኤርትራ አስተባባሪ ከ2001 እስከ 2002 በግንባሩ የሶማሊያ አስተባባሪ ከ2003 እጃቸውን እስከሰጡበት ቀን ድረስ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴና የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሀላፊ ሆነው የግንባሩን ተልዕኮ ሲያስፈፅሙ ቆይተዋል።

ሰሞኑን በሶማሊ ክልል ዋርዴር በኩል እጃቸውን ለኢትዮጵያ መንግስት የሰጡት አቶ አደን በስፍራው ለሚገኘው የዋልታ ሪፖርተር እንደተናገሩት የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር የቆመለትን ዓላማ ወደ ጎን በመተው ሙሉ በሙሉ የሻዕቢያ ተላላኪ በመሆኑና ህገ ወጥ አሰራር በውስጡ በመንገሱ የተነሳ ግንባሩን ጥለው ለመኮብለል ተገደዋል።

ግንባሩ የአንድ ጎሳ ስብስብና ከኢትዮጵያ ጠላቶች ሁሉ ያበረ ከመሆኑም በላይ በነፃ አውጪ ስም የተቋቋመ የግለሰቦች ሀብት ማካበቻ እየሆነ መምጣቱን አቶ አደን ተናግረዋል።

በነዚህ ውስጣዊ ቀውሶች ምክንያት በአሁኑ ሰአት ግንባሩ ለሁለት ተሰንጥቆ ኤርትራ ውስጥና ሀገር ውስጥ በሚገኝ ጎራ ለይተው በሁለት የሬድዮ ጣቢያዎች እየተወዛገቡ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

የዋርዴር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዩሱፍ ጣሂር ሆሽ በበኩላቸው ግለሰቡን የዋርዴር ከተማ ህዝብና መስተዳድሩ በሰላም ተቀብለው በማስተናገድ ላይ ሲሆኑ በአሁኑ ሰአት በአካባቢው ስለ ግንባሩ ጸረ ህዝብ ተግባራት ለህዝቡ ትምህርት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል የሱማሌ ክልል ህዝብና ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎች ኦኤን ኤል ኤፍ ከአፍራሽ ተልዕኮው ተቆጥቦ ወደ ሰላማዊ መድረክ እንዲመጣና ከሻዕቢያ ጋር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።

የአቶ አደን ዩሱፍን እግር ተከትለው በርካታ መሳሪያ ያነገቱ የግንባሩ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ኑሮ እየተመለሱ መሆናቸው የክልሉ የፀጥታና ፍትህ ማስተባበሪያ ጠቅላይ ቢሮ ሀላፊ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።