|
ሆላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የጀመረችውን ኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እየተንቀሳቀሰች ነው |
አዲስ አበባ ጥቅምት 9/1999/ዋኢማ/ ሆላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የጀመረችውን የንግድና ኢንቨስትመንት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከርና ለማስፋፋት እየተንቀሳቀሰች መሆኑን በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ገለፁ። በሆላንድ የመኪና መገጣጠሚያ ኩባንያ በ20 ሚሊየን ብር መነሻ ካፒታል በሞጆ ከተማ የተቋቋመው የቤት መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ማምረት ጀመረ። በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ አምባሳደር ሚስተር አልፖንስ ሂኒክንስ ትናንት ማምሻውን በሆላንድ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገጣጥማ ለገበያ የቀረበችው "ዶክ" የተሰኘች የቤት አውቶሞቢል ምረቃ ስነ ስርዓት ላይ እንደገለፁት፤ ሆላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ የኢንቨስትመንትና የንግድ ግንኙነት መመስረት ትፈልጋለች። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ፣ አውሮፓና ለመካከለኛው ምስራቅ አገራት በቅርብ የምትገኝና ለገበያ አመቺ በመሆኗ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራትን የኢንቨስትመንት ትስስር አጠናክራ የመቀጠል ፍላጎት እንዳላት ገልጸው፤ በኢንቨስትመንት መስክ በጋራ ለመስራት በሁለቱ ሀገራት መካከል በተደረሱ ስምምነቶች መሰረት የሁለቱም ሀገራት ባለሀብቶች በሽርክና ያቋቋሙት የቤት መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ወደ ማምረት ተግባር መሸጋገሩን ገልፀዋል። አገራቸው በተጨማሪም በንግድ፣ ኢንዱስትሪና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ባላት ፍላጎት መሰረት የተለያዩ ስምምነቶችን ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን አምባሳደር ሂኒክንስ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ሆላንዳዊያን ባለሀብቶችን ለመሳብ ኤምባሲያቸው ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንም አመልክተዋል። የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ ሚስተር ዊ ገንስ በበኩላቸው ፋብሪካው ከተያዘው ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ አንድ ሺ መኪናዎችን በመገጣጠም ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቀዋል። ፋብሪካው የሚያመርታቸው መኪናዎች ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ ለጅቡቲ፣ ኬኒያ፣ ደቡብ አፍሪካና የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ገበያዎች ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ጠቅሰው፤ የፋብሪካው በኢትዮጵያ ውስጥ መቋቋምም ሀገሪቱ ቀደም ሲል ከውጪ ተሽከርካሪ ለማስገባት ታወጣ የነበረውን የውጪ ምንዛሪ ለማስቀረት እንደሚያግዛት አስረድተዋል። ኢትዮጵያዊው የፋብሪካው ሸሪክ ባለሀብትና የኦፕሬሽን ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ታደሰ ተሰማ በበኩላቸው ፋብሪካው በሀገሪቱ እየተካሄደ ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ውስጥ ለኢኮኖሚው ዕድገትና ለኢንዱስትሪው ዘርፍ መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ያላቸውን ዕምነት ገልፀዋል። በፋብሪካው የሚመረቱት የቤት አውቶሞቢሎች ከአፍሪካና ከሀገራችን የመንገዶች ደረጃ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ጠቁመው፤ ለህብረተሰቡ በቀላሉ እንዲደርሱም በቅርቡ የዱቤ ሽያጭ እንደሚጀምር መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። የፋብሪካው የመጀሪያ ምርት የሆነችው መኪና ትናንት በሂልተን ሆቴል በይፋ በተመረቀችበት ወቅት የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎች ተገኝተዋል። |
|
|
|
|