በኢትዮጵያ የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ባህል እያደገ መምጣቱን ተገለጸ

አዲስ አበባ ጥቅምት 9/1999/ዋኢማ/ ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ባህል እያደገ በመምጣቱ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ህዝብ የሁለት ቢሊዮን ብር ብድር ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ማይክሮፋይናንስ ተቋማት ዳይሬክተር ገለጹ። የአዲስ አበባ ብድርና ቁጠባ ተቋምም በመጀመሪያው የሩብ ዓመት ለደንበኞቹ 18 ሚሊየን 500 ሺ ብር ብድር መስጠቱንና አዲስ የማይክሮ ባንክ አገልግሎት መጀመሩን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ማይክሮፋይናንስ ተቋማት ዳይሬክተርና የአፍሪካ ማክሮ ፋይናንስ ኔትዎርክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ወልዳይ አምሐ ትናንት ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ተቋሙ በአገሪቱ የብድርንና ቁጠባን ባህል ለማስፋፋት ባደረገው እንቅስቃሴ በህብረተሰቡ ተበድሮ አትራፊ በሆኑ ተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች የመሰማራት ፍላጎት እያደገ መጥቷል።

በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ብቻ በአገሪቱ በሚገኙ 27 የብድርና ቁጠባ ተቋማት አማካይነት 1 ነጥብ 7 ሚሊየን የሚሆን ህዝብ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም በአገሪቱ ከሚገኙ ቤተሰቦች 17 ከመቶ የሚሆን ድርሻ መያዙን ተናግረዋል።

የገንዘብ ተቋማቱ ከህዝቡ ጋር ተባብረው በመስራታቸውና ታኣማኒነትን ማትረፍ በመቻላቸው በበጀት ዓመቱ የሁለት ቢሊየን ብር ብድር መስጠታቸውንና ተበዳሪዎችም በወሰዱት ገንዘብ ውጤታማ ስራ በመስራት ላይ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

በዚህም ከ90 እስከ 95 በመቶ የሚሆኑ ተበዳሪዎች በኑሯቸው ላይ ለውጥ ማምጣት መቻላቸውን ከአሜሪካና ኖርዌይ ዩኒቨርስትዎች በመጡ ባለሙያዎች በተደረገ ጥናት መረጋገጡን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ጊዜ የብድር ተቋማቱ ደንበኞች የወሰዱትን ብድር በወቅቱ ከመመለሳቸው በተጨማሪ 707 ሚሊየን ብር ያህል በቁጠባ ሒሳብ ማስቀመጣቸውን የተናገሩት ዶክተር ወልዳይ፤ ሁኔታው በህብረተሰቡ የቁጠባ ባህል እየጎለበተ መምጣቱን ያመላክታል ብለዋል።

የብድርና ቁጠባ አገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ከተቋማቱ ጋር በቅርበት መስራት በመቻላቸው ከሚወስዱት ብድር ውስጥ ከ95 እስከ 98 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ በወቅቱ በመመለስ ላይ እንደሚኙም አመልክተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ብድርና ቁጠባ ተቋም በተያዘው የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ አጋማሽ ለደንበኞቹ 18 ሚሊየን 500 ሺ ብር ብድር መስጠቱንና አዲስ የማይክሮ ባንክ አገልግሎት መጀመሩን የተቋሙ ህዝብ ግንኙነት መኮንን አቶ ሲሳይ ወርቅነህ ገልጸዋል።

የህዝብ ግንኙነት መኮንኑ እንደገለጹት፤ ተቋሙ ብድሩ የሰጠው ባለፉት ሶስት ወራት በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ስራዎች ለተሰማሩ 4 ሺ 564 ደንበኞቹ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ከግማሽ የሚበልጡት ሴቶች ናቸው።

የብድር አገልግሎቱ የሚሰጠው በአዲስ አበባ የሚታየውን ድህነትና ስራአጥነተ ለመቅረፍ ታስቦ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሲሳይ፤ የተሰጠው ብድር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር ከ90 በመቶ በላይ ብልጫ ያለው ሲሆን የተበዳሪው ቁጥር በዛው ልክመጨመሩን አስረድተዋል።

ተቋሙ በሚቀጥሉት ዘጠኝ ወራትም ከ450 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ለመስጠት ማቀዱንና ከ100 ሺ በላይ ተበዳሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

ተቋሙ በአዲስ አበባ አንድ የማይክሮ ባንክ ከፍቶ በመንቀሳቀሰ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ መስተዳድር ስር ተቀጥረው በማገልገል ላይ ላሉ የመንግስት ሰራተኞች የብድርና የቁጠባ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ባንኩ በከተማዋ የተወሰነ ገቢ ላላቸውና ለመንግሰት ሰራተኞች ለመኖሪያ ቤት መስሪያ እንዲሁም ለሌሎች ፍጆታ የሚሆን ብድር መስጠት መጀመሩን ገልጸው፤ የባንኩ መመስረት በከተማዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር በማቃለል ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ማስረዳታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።