ሮተሪ ኢንተርናሽናል የጸረ ልጅነት ልምሻ የክትባት ዘመቻን ለማጠናከር ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታወቀ

አዲስ አበባ ጥቅምት 8/1999/ዋኢማ/ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለሚያካሂደው የጸረ ልጅነት ልምሻ መደበኛ ክትባት ዘመቻ ድጋፍ የሚሰጡ 99 የሮተሪ ኢንተርናሽናል አባላት በመጪው ቅዳሜና ዕሁድ በ13 ወረዳዎች የቤት ለቤት ግንዛቤ ለማስጨበጥና ክትባት ለመስጠት ዝግጅት ማድረጋቸውን በሮተሪ ኢንተርናሽናል የብሔራዊ ፖሊዮ ኮሚቴ አስታወቀ።

በሮተሪ ኢንተርናሽናል የብሔራዊ የልጅነት ልምሻ ኮሚቴ ሊቀ መንበር አቶ ናሁሰናይ አርአያ ትናንት በሳንጋም ሬስቶራንት በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ መደበኛ የልጅነት ልምሻና የፀረ ስድስት ክትባቶች ዘመቻን ለማጠናከር አባላቱ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ 12 ወረዳዎች ህብረተሰቡን በመቀስቀስና ክትባት በመስጠት ድጋፍ ያደርጋሉ።

በወረዳዎቹ ለሚደረገው ዘመቻ ከካናዳና ከአሜሪካ የመጡ 64 የሮተሪ ኢንተርናሽናል አባላት እንደሚሳተፉ ገልጸው፤ 12 ሺ ያህል ህጻናት ክትባቱን እንደሚያገኙ አመልክተዋል።

በመንግስት፣ በዓለም ጤና ድርጅት፣ በሮተሪ ኢንተርናሽናልና በዩኒሴፍ የጋራ ጥረት ኢትዮጵያን ከልጅነት ልምሻ ነጻ ማድረግ ተችሎ እንደነበር ጠቅሰው፤ ሆኖም ባለፈው መጋቢት በሱዳን ተዋሳኝ አካባቢ አንድ የፖሊዮ ምልክት መታየቱን ተከትሎ በአማራ፣ ትግራይ፣ ምስራቅ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች 39 በልጅነት ልምሻ መሰል በሽታ የተጠቁ ህጻናት መገኘታቸውን ተናግረዋል።

ይህም ካሁን ቀደም በተደረጉ የክትባት ዘመቻዎችና በመደበኛው የፀረ ስድስት ክትባት ፕሮግራም ያልተከተቡ ህጻናት መኖራቸውን እንደሚያመለከት አስረድተዋል።

የልጅነት ልምሻን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ሮተሪ አንተርናሽናል የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጡት አቶ ናሁሰናይ፤ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ መደበኛ ክትባት መስጫ ጣቢያዎች በማምጣት እንዲያስከትቡ ጥሪ ማቅረባቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።