ለውጭ ገበያ የሚላከው የቁም እንስሳትና የስጋ ምርት አቅርቦትን ለማሳደግ አዋጭ የሆነ መንገድ መከተል እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ ጥቅምት 8/1999/ዋኢማ/ ለውጭ ገበያ የሚላከው የቁም እንስሳትና የስጋ ምርት አቅርቦትን በተያዘለት ዕቅድ ለማስኬድ አዋጭ የሆነ መንገድ መከተል እንደሚገባ የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ። በተያዘው የመጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት ከ39 ሺ በላይ የቁም እንስሳትና የከ1 ሺ 200 ቶን በላይ ስጋና የስጋ ውጤቶች ወደ ተለያዩ ዓለም አገራት መላካቸው ተገልጿል።

የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ያዕቆብ ያላ የቁም እንስሳትና ስጋ ኤክስፖርት የ1998 አፈፃፀምና የ1999 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የገበያ ሪፖርት አስመልክቶ ዛሬ በቡናና ሻይ አዳራሽ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ እንደገለፁት፤ በዘርፉ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሀብቶች የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖራቸው ለማስቻል ገበያውን በመረጃ የተደገፈ ማድረግ ይገባል።

በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከታየው ግምገማ መሰረት በቁም እንስሳት ገበያ የተሻለ አፈፃፀም የታየ ሲሆን፤ በስጋና የስጋ ውጤቶች ግን ከዕቅድ በታች የሆነ አፈፃፀም መመዝገቡን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

ለዚህም አዳዲስ በመገንባት ላይ ያሉ ቄራዎች በዕቅዳቸው መሰረት ተጠናቀው ስራ አለመጀመራቸው ዋነኛ ምክንያት ሲሆን፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂን ተጠቀሞ ስጋን መላክ አለመጀመር፣ ደረጃቸውን የጠበቀ የኳራንቲን አገልግሎትና የማድለቢያ ጣቢያዎች አለመኖር እንዲሁም የእንሰሳት አቅርቦት ዕጥረትና ላኪዎች የሚከፍሉት ዋጋ ከጠረፍ የኮንትሮባንድ ንግድ ዋጋ ጋር ተወዳዳሪ አለመሆን አስተዋፅኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።

በመሆኑም በተቀሩት ሶስት ሩብ ዓመታት ገበያ መር መረጃን በማሰባሰብና የንግድ አቅጣጫን በመቀየር የተያዘው ዕቅድ ተፈፃሚ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት መደረግ እንዳለበት አስገንዝበው፤ ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በውይይቱ በቀረበው ሪፖርትም በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ወደ ተለያዩ የአፍሪካና አረብ ሀገራት 39 ሺ 591 የቁም እንስሳት 1 ሺ 222 ቶን ስጋና የስጋ ውጤቶች መላካቸውን ተመልክቷል።

ወደ ውጪ የተላኩት የቁም እንስሳትና ስጋ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በቁም እንስሳት የ32 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ ሲኖረው፤ በስጋና ስጋ ውጤቶች 44 ነጥብ 5 ከመቶ ማነሱን በሪፖርቱ መግለፁን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።