ሥርዓተ- ጾታን ማዕከል ያደረገ የልማት እንቅስቃሴ ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ

አዳማ ጥቅምት 8/1999/ዋኢማ/ ሥርዓተ ጾታን ማዕከል አድርጎ የሚተገበር ማንኛውም የልማት እንቅስቃሴ ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ድርሻ እንዳለው የውሀ ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የሴቶች ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ላቀች ኃይሌ በገጠር መጠጥ ውሀና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች ሥርዓተ-ጾታን ለማካተት የተዘጋጀ የአሰልጣኞች ስልጠና በአዳማ ከተማ ሲጀመር እንዳስታወቁት፤ሌሎች የልማት ሥራዎችን ጨምሮ ሥርዓተ-ጾታን ያማከለ የገጠር መጠጥ ውሀና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች ለፈጣን ልማትና ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ድርሻ አለው።

ሴቶች የመጠጥ ውሀ ግንባታዎች ከመካሄዳቸው በፊት በዕቅድ አወጣጥ፣በቦታ መረጣ፣በውሀ ክፍፍልና ግምገማ ላይ ተሳትፏቸው ቢጎልበት የንጹህ መጠጥ ውሀ ብክነትን ለማስቀረትና የውሀ ሽፋንን ለማሳደግ እንደሚያስችል ኃላፊዋ አስታውቀዋል።

ሴቶች ተከታታይ ስልጠና አግኝተው በሥራው ሁለገብ ተሳትፎ ቢያደርጉ በጥገና ምክንያት፣በመቅጃ ዕቃዎችና በአቀዳድ ጉድለቶች የሚባክነውን የውሀ መጠን በመቀነስ ረገድ አስተዋፅዖአቸው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

በሚኒስቴሩ ተዘጋጅቶ የቀረበው የሥራ መመሪያም እነዚህን ችግሮች የሚያስወግድ በመሆኑ በትክክል ወደ ተግባር ሊተረጎም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የብሔራዊ የውሀ ሀብት ልማት አስተዳደር ፖሊሲን መሰረት ያደረገ ስትራቴጂና የልማት ፕሮግራሞችን በመንደፍ ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ወይዘሮ ላቀች፤ሴቶችም በልማቱ ዘርፍ እኩል ተሳትፎ አድርገው የልማት ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው አስገንዘብዋል።

የውሀ ክፍለ ኢኮኖሚውን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ በመሆኑ በተለይ ሴቶች ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ተሳትፏቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው አስረድተዋል።

በተጨማሪም ሴቶች በአካባቢያቸው በሚቆፈሩት መፀዳጃ ቤቶች ሥራ ላይ እኩል ተሳትፎ በማድረግ የልጆቻቸውንም ሆነ የራሳቸውን ሕይወት ሊታደጉ እንደሚገባቸው ገልጸው፤የስልጠናው ተሳታፊ ባለሙያዎች ወደየአካባቢያቸው ሲመለሱ ሕብረተሰቡን ማስተማር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ትናንት በተጀመረውና ለሦስት ቀናት በሚቆየው የአሰልጣኞች ስልጠና ከሰባት ክልሎች የተውጣጡ የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ተወካዮች፣የየክልሎቹ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ተወካዮች፣የሕዝብ ግኑኝነት ባለሙያዎች ፣የሕብረተሰብ ተሳትፎ አደረጃጀት ተወካዮችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።