ኢህአዴግ ለአባላቱ የአመራር ስልጠና እንደሚሰጥ ገለጸ

አዲስ አበባ ጥቅምት 8/1999/ዋኢማ/የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ብቃትና ጥራት ያለው አመራር ለመፍጠርና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያስችል ተከታታይ የአመራር ስልጠና እንዲሚሰጥ አስታወቀ።የመጀመሪያው ዙር የከፍተኛ አመራር አካላት ስልጠና ጥቅምት 15 እንደሚጀመር ተገልጿል።

በጽሕፈት ቤቱ የስልጠናና አባላት አቅም ግንባታ ዋና ክፍል ኃላፊ አቶ ሰይፈ ክንፉ እንደገለፁት፤ዘላቂ ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ የሚያግዝ የአመራር ስልጠና በተከታታይ ፕሮግራሞች ለአባላት ይሰጣል።

በሶስት ዙር ለአንድ ወር በሚሰጠው ስልጠና የመጀመሪያ ዙር ከፍተኛ አመራሮች የሚሰለጥኑ ሲሆን፤ስልጠናውን ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን ኃላፊው አስታውቀዋል።

ስልጠናው የአመራር አባላቱ ብቃት ያለው አመራር ለመስጠት፣የመልካም አስተዳደር እምርታን ለማስመዝገብና በውጤት የሚለካ ስራ ለመስራት እንዲችሉ ያግዛቸዋል ብለዋል።

ኢህአዴግ ዘንድሮ ከአራት ሚሊየን አባላቱ መካከል አስር በመቶ ለሚሆኑት የአመራር ስልጠና ለመስጠት ማቀዱን የጠቆሙት ኃላፊው፤የተጀመረውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራ ቀጣይ ለማድረግ ብቁ አመራር ወሳኝ በመሆኑ የአመራር ስልጠና መስጠት የዓመቱ ቁልፍ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል።

ለአመራር አባላቱ የሚሰጠው ስልጠና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመርና ሳይንሳዊ የአመራር ጥበብን ከዓለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ሲሆን፤መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አቶ ሰይፉ ተናግረዋል።

በየደረጃው ያሉ የድርጅቱ አመራር አካላት በተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው የሚመዘኑ በመሆኑ ለስልጠናው ትኩረት ሰጥተው የተጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ማስገንዘባቸውን ዛሬ የታተመውን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋዜጣ ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።