|
በሱማሌ ክልል የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኛ አመራር መፈጠር እንደሚገባ ተገለጸ |
ጅጅጋ ጥቅምት 8/1999/ዋኢማ የሱማሌ ክልል የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኛ አመራሮች መፈጠር እንዳለባቸው የክልሉ ርዕስ መስተዳድር ገለፁ። ለክልሉ ካቢኔ አባላትና የቢሮ ኃላፊዎች የተዘጋጀው የ1999 የጀበት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ትናንት ሲጠናቀቅ የክልሉ ርዕስ መስተዳደር አቶ አብዱላሂ ሐሰን ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ የክልሉን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ ለማድረግ የስራ ተነሳሽነት ያለው ቁርጠኛ አመራር መፍጠር ይገባል። በመጀመሪያ ሩብ ዓመቱ በዋናዋና ቢሮዎች ላይ በተካሄደው የስራ ግምገማ አንዳንድ የቢሮዎች ስራን በአግበቡ ያለመስራት፣ በሰው ሀይል አስተዳደርና በዕቅድ አፈፃፀም ላይ ችግሮች የታዩባቸው ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ ስር የሰደደውን የህዝብ ችግር ለመፍታት አበረታች እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ገልፀዋል። አንዳንድ ቢሮዎችም ለወረዳዎች የተጠናከረ ድጋፍ ያለመስጠት፣ የቁጥጥርና ክትትል ስርዓት ያለመርጋትና የአቅም ውስንነት ችግሮች እንደሚስተዋልባቸው ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። ችግሩንም ለመፍታት መንግስት በተያዘው የበጀት ዓመት በስምንት ቢሮዎች ስራና ሰራተኛን የሚያገናኝ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም በአፋጣኝ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሜቴ በክልሉ ካቢኔ መሰየሙን ገልጸው፤ በተቀሩት ቢሮዎች ላይም የማስተካከያው ዕርምጃው ደረጃ በደረጃ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። ዋናው የልማቱ ተጠቃሚና የልማቱ ኃይል የሚገኘው በወረዳዎች በመሆኑ የክልሉ ቢሮዎች በመረጃ የተጠናከረ መዋቀር ዘርግተው ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተጠናከረ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል ተከታታይ የዓቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥ ርዕስ መስተዳድሩ ገልፀዋል። ስልጠናው በክልሉ ዓቅም ግንባታ ቢሮ፣ የክልሉ ስራ አመራርና የልማት ኢንስቱቲዩትና በፌደራል መንግስት ባለሙያዎች አማካኝነት ለመስጠት አስፈላጊውን ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ በክልልና በወረዳ ደረጃ በካፒታልና በመደበኛ በጀት ለሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ከ700 ሚሊየን ብር በላይ በጀት መድቦ እንቅስቃሴ መጀመሩን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸው፤ በክልሉ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር በመዘርጋት ቁርጠኛ አመራር ለመፍጠር የተጀመረውን ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማስረዳታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|