|
ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዕቅድ ማዘጋጀቱን ገለጸ |
መቀሌ ጥቅምት 8/1999/ዋኢማ/ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ብቁ የተማረ ዜጋ ለማፍራት የሚያስችል የ20 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አውጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን አስታወቀ። የዩኒቨርሲቲው ፕረዝዳንት ዶክተር ምትኩ ኃይለ በትግራይ ማስታወቂያ ቢሮ በየሦስት ወሩ ከሚታተመው መቓልሕ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ስትራቴጂክ ዕቅዱ በዩኒቨርሲቲው የሚታዩ ችግሮችን ለማስወገድ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸው፤የመማር ማስተማር ሂደቱን ተማሪን ያማከለ በማድረግ ተማሪው ብቁ ዜጋ ሆኖ የሚወጣበትን መንገድ የሚያመቻች መሆኑን አስታውቀዋል። ዕቅዱ መምህራን ጥራት ያለው ትምህርት የሚሰጡበትን አቅጣጫ የሚጠቁም፣ዩኒቨርሲቲው የምርምር ሥራዎችን እንዲያከናውንና በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ጉዳዮች ከህብረተሰቡ ጋር ተባብሮ እንዲሰራ የሚያስችል ነው ብለዋል። በዩኒቨርሲቲው ከሚታዩት ዓበይት ችግሮች መካከል ልምድና ብቃት ያለው ስታፍ አለመኖር፣የተዝረከረከ የሃብት አስተዳደር ፣ደካማ የፈተና ምዝና ዘዴ፣ግልጽ ያልሆነ ግዢ መፈጸምና የመሳሰሉት እንደሚገኙበት ዶክተር ምትኩ አስረድተዋል። ስትራተጂክ ዕቅዱ እነዚህን ችግሮች ደረጃ በደረጃ የሚፈታ እንደሆነም ዶክተር ምትኩ ገልጸዋል። በተጨማሪም መምህራን ከተማሪዎቻቸው ጋር መልካም ግንኙነት እንዲመሰርቱና ለትምህርቱ ሥራ በቂ ጊዜ እንዲሰጡ የሚያስችሉ ተግባራትም ይከናወናሉ ብለዋል። በመምህራን በኩል የሚታዩ የነጥብ አሰጣጥና የሥነስርዓት ችግሮችን ለመፍታትም በየፋካሊቲውና ትምህርት ክፍሉ ግምገማ በማካሄድ የሥራ ጥራት እንዲረጋገጥ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ፕረዝዳንቱ አስረድተዋል። በሌላ በኩል የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ግምገማ አድርጎ የማኔጅመንት ለውጥ በማድረግ ሁለት ምክትል ፕረዝዳንቶችን በሌላ እንዲተኩ ማድረጉን ተናግረዋል። ከኃላፊነታቸው የተወገዱት ምክትል ፕረዝዳንቶች መልካም አስተዳደርን በማስፈንና የሙስና ችግሮች በመዋጋት በኩል ችግሮች እንደነበሩባቸው ስለተረጋገጠ በአጥፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ጉዳያቸውን የዩኒቨርሲቲው የህግ ፋካሊቲ እንዲመረምረው ቦርዱ ውሳኔ ማስተላለፉን መናገራቸውን መቃልሕ መጽሔትን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|