|
የዓለማችን የመጨረሻው ግዙፍ የተባለው የኤርባስ አውሮፕላን በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያ ሜዳ ላይ አረፈ |
|
በኢትዮጵያ የኤርፖርቶች ድርጅት የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ስራ አስኪያጅ አቶ ሃይላይ ገብረፃዲቅ የኤርባሱን አዲስ አበባ ማረፍ አስመልክተው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደተናገሩት፤ የኤርባሱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የአየር ማረፊያውን ዓለም አቀፍ ብቃትና ተወዳዳተሪነት ያረጋግጣል። በዘመናችን የአየር ትራንስፖርት እጅግ ዘመናዊና ግዙፍ የሆነው ኤርባስ 380/861 የንግድ አውሮፕላን 560 ቶን ነጠላ ክብደት፣ 400 ቶን የመጫን ዓቅም 22 ጎማዎች ያሉት ሲሆን፤ የበረራ አስተናጋጆችን ሳይጨምር በአንድ ጊዜ 555 መንገደኞችን የማጓጓዝ ብቃት እንዳለው ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል። በተጨማሪም አውሮፕላኑ 80 ሜትር በ80 ሜትር ስፋትና ርዝመት ሲኖረው፤ ከመሬት 24 ነጥብ 1 ሜትር ርቀት አለው። በጀርመን፣ በእንግሊዝና በፈረንሣይ ኤርባሶች አማካኝነት የተመረተው አውሮፕላኑ ከአፍሪካ ለሙከራ ያረፈው በኢትዮጵያ ብቻ መሆኑ ለአገሪቱ ትልቅ ኩራት ነው ያሉት አቶ ሃይላይ፤ ለዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዕድገት ደረጃና አልቲትዩድ ከ7 ሺ 500 ጫማ በላይ መሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል። ለሙከራ በረራ ከፈረንሣይ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ይኸው አውሮፕላን ለአምስት ቀናት በቀን ሁለት ጊዜ በመነሳትና በማረፍ የነዳጅ አጠቃቀሙንና የበረራ ዓቅሙን የመፈተሽ ሥራ እንደሚያከናውን ጠቁመው፤ ይኸንን የሚያረጋግጡ ከአውሮፕላኑ ጋር የመጡ ከ45 በላይ ኢንጂነሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዳሉም ተናግረዋል። በዚህ ቆይታውም ኤርባሱ በሚያገኘው አገልግሎት ለኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትና ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚከፍልም ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዕለት ወደ ዕለት ብቃቱንና ጥራቱን እያስመሰከረ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን፤ ለዚህም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1 ሚሊየን 700 ሺ መንገደኞች ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ ዓለም አገራት ማመላለሱ ገልጸዋል። በቅርቡ ወደ ሥራ በገባበት የካርጎ ገበያም አየር መንገዱ ከ500 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ያገኘ ሲሆን፤ ገበያው በፍጥነት እያደገ እንደሚገኝ ከአየር መንገዱ የተገኘውን መረጃን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|