ቢሮው ከ16ሺ በላይ ወገኖች የፀረ ኤች አይቪ መድሃኒት በነፃ እየሰጠ መሆኑን ገለፀ

አዲስ አሰበባ ጥቅምት 2/1999/ዋኢማ /ከኤችአይቪ/ኤድስ ጋር ለሚኖሩ ከ16ሺ በላይ ወገኖች የፀረ ኤች አይ ቪ /ኤድስ መድሃኒት በ15 የጤና ማዕከላት በነፃ በመሰጠት ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ ።

በቢሮው የተላላፊ በሽታዎች መቆጣጠሪያና የጤና ፕሮግራሞች ሀላፊ ዶክተር አቻምየለህ አለባቸው ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤በከተማው ውስጥ ከሚገኙት 23 የጤና ማዕከላት መካከል በ15ቱ ነፃ የኤች አይቪ መድሃኒት መስጠት የተጀመረ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት ሁለት ተጨማሪ የጤና ማዕከላት አገልግሎቱን ይጀምራሉ።

ቢሮው አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ከመጋቢት 1997 ዓም ጀምሮ ከተለያዩ ክልሎች የመጡትን ጨምሮ ለ21 ሺ112 ሰዎች አገልግሎት የሰጠ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 16ሺ 400 የሚሆኑት ከአዲስ አበባ መሆናቸውን ገልፀዋል።

አያይዘውም በቢሮው እሰከ መጪው ታህሳስ ወር ድረስ ለ19 ሺ ህሙማን የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ማቀዱን ጠቁመው፤ እስከ አሁን ከዕቅድ በላይ መሰራቱን ተናግረዋል።

እንዲሁም ወደ 47 ሺ የሚጠጉ ሰዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት ሀላፊው አገልግሎቱን ለማስፋፋት ብዙ መስራት እንደሚገባም ገልፀዋል።

በቢሮው ስር የሚገኙ ሁሉም ሆስፒታሎች አገልግሎቱን በመስጠት የቆዩ ቢሆንም የተጠቃሚዎቹን ቁጥር ለማሳደግ በጤና ጣቢያ ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉን ገልፀው፤ ወደፊት በግል የጤና ተቋማትም አገልግሎቱ እንዲሰጥ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በጤና ጣቢያዎች ውስጥ አገልግሎት ለመስጠት የሰው ሀይል ስልጠና፣ የመድሃኒት አቅርቦትና እና በቁሳቁስ የሟሟላት ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ስራ መገባቱን ገልፀዋል።

ቢሮው የግንዛቤ ችግሮችን ለመከላከል መጠነ ሰፊ የህብረተሰብ ንቅናቄ ፕሮግራም በማካሄድ ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ በፕሮግራሙ ተነሳስተው የሚመጡ ህሙማን የአገልገሎቱ ተጠቃሚዎች እየሆኑ እንደመጡ መግለፃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።