|
ሰዎች ለሰዎች ከክልሉ ጽህፈት ቤትጋር የ39 ሚሊየን ብር የእርዳታ ስምምነት ተፈራረመ |
አዲስ አበባ ጥቅምት 2/1999/ዋኢማ/ የአማራ ክልል የምግብ ዋስትናና አደጋ መከላከል ጽህፈት ቤት የአሳግርት ወረዳን የልማት እንቅስቃሴ የሚያግዝ የ39 ሚሊዮን ብር የልማት ስምምነት ሰዎች ለሰዎች ከተባለ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር ተፈራረመ፡፡የልማት ስምምነቱ ለሶስት አመታት የሚቆይ ሲሆን 54 ሺ ሰዎቸን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ዛሬ በሰዎች ለሰዎች ግብረሰናይ ድርጅት ጽህፈት ቤት በተደረገው የልማት ስምምነት የፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ የአማራ ክልል የምግብ ዋስትናና አደጋ መከላከል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በአምላኩ አስረስ እንደገለጹት፤ በክልሉ በአሁኑ ወቅት 128 አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጀቶች 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በሆነ ወጭ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እያካሄዱ ነው፡፡ በግብረሰናይ ድርጅቶቹ እየተካሄዱያሉት 284 ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ኃላፊው ገልፀው፤በዚህም 14 ሚሊዮን የሚጠጉ የክልሉ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡ የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት በክልሉ ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት ከሚሰሩት ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ግንባር ቀደም እንደሆነ ጠቁመው ፤በዚህም በሰሜን ሸዋ ዞን አሳግርት ወረዳ የሚገኘውን የልማት እነቅስቃሴ ለማገዝ የ39 ሚሊዮን 514 ሺ ብር የእርዳታ ስምምነት ዛሬ ተፈራርሟል። በጀቱ በምግብ ዋስትና፣ በጤና፣ በትምህርትና ለተለያዩ የልማት ስራዎች የሚውል መሆኑን ገልፀው፤ በሚከናወኑት የልማት ስራዎች ከ 54 ሺ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡ የሰዎች ለሰዎች ግብረሰናይ ድርጅት መስራችና ሊቀመንበር ዶክተር ካርል ሄንዝ ቦም በበኩላቸው፤ ስምምነቱ የወረዳውን ህዝብ የምግብ ዋስትና፣ የጤናና የትምህርት ችግር ለማቃለል የሚረዳ መሆኑን ገልፀው ፤ በልማት ስራው የአካባቢው ነዋሪ በሁሉም ረገድ ተለውጦ ማየት እንደሚመኙ ተናግረዋል፡፡ የልማት ስምምነቱን ለማድረግ እርዳታ ያደረጉላቸው አለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶችን አመስግነው፤ በቀጣዩም ድርጅቱ በዋናነት ከሚንቀሳቀስባቸው ከኦሮሚያና አማራ ክልሎች በተጨማሪ ሌሎች ክልሎች የሚያደርጉትን የልማት እንቅስቃሴ ለማገዝ ቃል ገብተዋል፡፡ በስምምነቱም በክልሉ በቀጣዮቹ ሶስት አመታት በግብርና ፣ በትምህርት፣ በውሃ ልማት፣በሴቶች የልማት እንቅስቃሴ፣ በስነተዋልዶና በኤች አይ ቪ መከላከል ዙሪያ ህብረተሰቡን በቀጥታ የሚያሳትፉ ፕሮጀክቶች እንደሚከናወኑ ዶክተር ካርል መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡ |
|
|
|
|