|
ወደ ኬኒያ የሚፈልሱ የሶማሊያ ስደተኞች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱ ተገለፀ |
አዲስ አበባ ጥቅምት 2/1999/ዋኢማ/በሶማሊያ ያለው ውጥረት የሚባባስ ከሆነ በተያዘው የፈረንጆች አመት መጨረሻ ወደ ኬኒያ የሚፈልሱ የሶማሊያ ስደተኞች ቁጥር 80 ሺ ሊደርስ እንደሚችል አንድ የተባበሩት መንግስታት ባለስልጣን አስጠነቀቁ፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን የአስቸኳይ ጉዳይ ከፍተኛ ኃላፊና በሰሜን ምስራቅ ኬኒያ የሚገኘው የዳዳብ ስደተኞች ካምፕ ተጠሪ ሚስተር ጆፍ ወርድሌይ ትናንት ለሮይተርስ እንደገለፁት፤ አሁን ያለው የአፍሪካ ቀንድ በተለይ የሶማሊያ ውጥረት የሚባባስ ከሆነ 80 ሺ የሚደርሱ የሶማሊያ ስደተኞች ወደ ኬኒያ ይገባሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ በተያዘው ዓመት ድርቅንና የእስላማዊ አገዛዙን በመሸሽ እንዲሁም በሽግግሩ መንግስትና ሞቃዲሾንና የደቡብ ዳርቻን በተቆጣጠረው የእሰላማዊ ፍርድ ቤቶች ጥምረት መካከል ጦርነት ሊነሳ ይችላል በሚል ስጋት 35 ሺ ሶማሊያውያን ስደተኞች ወደ ዳዳብ የስደተኞች ካምፕ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ 162 ሺ ነዋሪዎች በሚኖሩባትና ከሶማሊያ ድንበር 100 ኪሜ ርቀት ላይ የሚገኘው የዳዳብ ስደተኞች ጣቢያ ሚገቡት የስድተኞች ቁጥር ባለፉት ሳምንታት በየቀኑ 1ሺ መድረሱን የገለጹት ተጠሪው በነሃሴ ወር በሁለቱ ወገኖች መካከል ባለው ተደጋጋሚ ግጭት ምክንያት የስደተኞች ቁጥር ሊጨመር እንደቻለ ተገምቷል። ካምፑ በተለይም በቅርቡ በእስላማዊ ህብረቱ ስር በወደቀችው የኪስማዩ ወደብ አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ በርካታ ስደተኞች እንደሚጎርፉና የምግብና የመጠለያ አገልግሎትን ለማዳረስ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ የእርዳታ ሰራተኞች ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለፃ የስደተኞቹን አመጣጥ በማየት ድርጅቱ እርዳታ የማከፋፈል ስራውን ባለ ሃይል ሁሉ ለማከናወን መዘጋጀታቸውንና በቅርቡም አዲስ ካምፕ መስራት እንደሚያስፈልግ ውሳኔ ላይ መደረሱ ኃላፊው መናገራቸውን ሮይተርስን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|