|
የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤት የመገናኛ ብዙሀንን የሚገድብ ደንብ ማውጣቱ ውግዘት ገጠመው |
አዲስ አበባ ጥቅምት 2/1999/ዋኢማ/ የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤት የመገናኛ ብዙሀንን የሚገድብ ደንብ ማውጣቱን እንደሚቃወም ዓለም አቀፍ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን አስታወቀ። የአሜሪካን ድምፅ ሬድዮ ትናንት በአማርኛ ዜና እውጃው እንደዘገበው በሶማሊያ ሞቃዲሾ የሚገኘው እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ምክር ቤት የመገናኛ ብዙሀንን አሰራር የሚገድብ 13 አንቀጾችን ያካተተ ደንብ ካለፈው እሁድ ጀምሮ ስራ ላይ ማዋሉ የፕሬስ ነጻነት የሚጥስ ተግባር ነው በማለት ድርጊቱን አውጉዞታል። ደንቡ እስልምናን የሚቃወምና በነዋሪዎችና በእስልምና ፍርድ ቤት መካከል የአመለካከት ልዩነት መኖሩን የሚቀሰቅሱ ዜና ነክ መረጃዎችን ስርጭትና ህትመት የሚያግድ እንደሆነ ሬድዮ ጣቢያው አትቷል። በተጨማሪም በሶማሊያ በሚገኙ መገናኛ ብዙሀን ከፍርድ ቤቶች የምዝገባ ፈቃድ አግኝተው እንዲንቀሳቀሱና የዜና ምንጮቻቸውን ቀደም ብለው እንዲታወቁ እንደሚያስገድድ ዘግቧል። እንዲሁም አሸባሪና ፅንፈኛ የሚሉ ቃላትን እንዳይጠቀሙ በደንብ ላይ ገደብ መጣሉን የጠቀሰው ሬድዮ ጣቢያው ህጉን ጥሰው በሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ላይ ስለሚወሰድባቸው እርምጃ ዘገባው ያለው ነገር የለም ሲል ሬዲዮ ጣቢያውን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል አመልክቷል። |
|
|
|
|