ዩኒሴፍ በሕፃናት ጤና ክብካቤ የሚየካሂደውን ድጋፍ በአሥር እጥፍ ሊያሳድግ ነው

አዋሳ ጥቅምት 2/1999/ዋኢማ/በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት /ዩኒሴፍ/በመጪው አዲስ የፈረንጆች ዓመት በሕፃናት መብትና ጤና ክብካቤ ዙሪያ በኢትዮጵያ የሚያካሂዳቸውን ፕሮጄክቶች በአሥር እጥፍ ለማሳደግ መዘጋጀቱን አስታወቀ።

በድርጅቱ የሕፃናት ጥበቃና የኤች አይ ቪ ኤድስ ዘርፍ ሃላፊ ሚስተር አለሳንደሮ ኮንትቺኒ በግሮግራሙ አሠራር ላይ ለመወያየት ትናንት በይርጋለም ከተማ በተጀመረው ዓውዶ ጥናት ላይ እንዳስታወቁት በመጠናቀቅ ላይ ባለው የፈረንጆች ዓመት ድርጅቱ በመደበው 10 ሚሊየን ብር በትግራይና ደቡብ ክልሎች ኤች አይቪ አድስን ለመከላከል ታስበው የተዘጋጁና ሥራ ላይ የዋሉ የናሙና ፕሮጀክቶች ውጤታማ ሆነዋል።

በየክልሎቹ በተመረጡ 20 ከተሞች ተግባራዊ በሆነው የሙከራ ፕሮጀክት በከፋ ድኅነት ውስጥ ለሚኖሩና ወላጅ አልባ ሕፃናት አሳዳጊ ለሆኑ እናቶች እሰከ 1ሺ ብር የሚደርስ ያለ ወለድ የሚከፈል ብድር በመስጠት በጥቃቅንና አነስተኛ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች በማሳተፍ ራሳቸውን እንዲችሉ መደረጉን ገልፀዋል።

በእንስሳት እርባታና ማድለብ፤ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም በአነስተኛ የንግድ ሥራ ዘርፎች ለመሠማራት ብድር ወስደው ወደ ሥራ የገቡ ሴቶች በአንድ ዓመት ውስጥ ራሳቸውን መቻላቸውንና ለልጆቻቸውም የተመጣጠነ ምግብ መስጠት እንደቻሉ በድርጅቱ ባለሙያዎች በተደረጉ ጥናቶች ለማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።

ለአንድ ዓመት በተካሄደው በዚሁ የሙከራ ፕሮግራም 12 ሺ ያህል ሴቶችና ሕፃናት ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው በመጪው አዲስ የፈረንጆች ዓመትም ፕሮግራሙን በአሥር እጥፍ በማሳደግ ፕሮጀክቶቹን በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት በትግራይ ፤ አማራ ፤ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች በተመረጡ አካባቢዎች ፕሮጀክቶቹን ለማካሄድ ከክልል እስከ ወረዳ ቢሮዎችን የመክፈትና አስተባባሪዎችን የመቅጠር ሥራ መካሄዱን ገልፀዋል።

የደቡብ ክልል የሕዝብ አደረጃጀት ተሳትፎና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ኪዳነማሪያም በበኩላቸው በመንግሥት የተነደፈውን የድኅነት ቅነሣ ስትራቴጅ በኤች አይ ቪ ኤድስና በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትና ሴቶች ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ በተደረገው ጥረት ዩኒሴፍ በክልሉ በተመረጡ አሥር ከተሞች 3ሺ ለሚሆኑ ሴቶችና ሕፃናት ድጋፍ ማድረጉን አረጋግጠዋል።

ድርጅቱ በቀጣይ በክልሉ ለሚያካሂዳቸው የልማትና የድኅነት ቅነሳ ሥራዎች ቢሮው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ዓውደ ጥናት 70 ያህል የተለያዩ መስሪያ ቤቶች፤ የዕድሮችና የኃይማኖት ተቋማት ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ በፕሮጀክቶቹ የአፈፃፀም መመሪያ ላይ ተወያይተው እንደሚያፀድቁ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።