በበጀት ዓመቱ በሁለት ቢሊየን ብር ወጪ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስቸሉ የልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/1999/ዋኢማ/ በተያዘው የበጀት ዓመት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚካሄዱ የተለያዩ የልማት ስራዎች ማስፈፀሚያ በፌዴራል መንግስት ሁለት ቢሊየን ብር ተመድቦ እንቅስቃሴ መጀመሩን በግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ቢሮ አስታወቀ። ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ በሚካሄደው የሰፈራ ፕሮግራም 40 ሺ የቤተሰብ መሪ አርሶ አደሮችን የተሻለ ለምነት ወዳላቸው አካባቢዎች በፈቃደኝነት ለማስፈር መታቀዱንም አመልክቷል።

በቢሮው የፕሮግራም ዝግጅትና ግምገማ መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ወልደሚካኤል ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ በምግብ ዋስትና ፕሮግራም በታቀፉ ስምንት ክልሎች በሚገኙ 285 ወረዳዎች የሚካሄዱት የልማት ስራዎች ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል አርሶ አደሩ በምግብ እህል ራሱን ለማስቻል የሚያግዙ ናቸው።

ለፕሮግራሙ ማስፈፀሚያ ከተመደበው በጀት ውስጥ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ህዝቦች፣ ሶማሌ፣ አፋርና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም ድሬዳዋ አስተዳደር ለመጀመሪያው ሩብ ዓመት የሚበቃ ገንዘብ ተለቆላቸው ልዩ ልዩ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

በክልሎቹ ቆላማና ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙና 321 ሺ የሚጠጉ አርሶ አደሮች በእንስሳት ዕርባታ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ንብ ማነብና ሌሎች የተቀናጁ የግብርና ልማት ፓኬጆች እንደሚሳተፉ አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል።

በፓኬጆቹ ተጠቃሚ የሚሆኑ አርሶ አደሮች ተስማሚና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው በመስኖ ልማት መሳተፍ እንዲችሉ የውኃ ጠብታ ቱቦዎች፣ የውኃ መሳቢያ ፓምፖችና ሌሎች የእርሻ መሳሪያዎችና የምርት ማሳደጊያ ግብአቶች እንደሚቀርብላቸው አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በገጠር አነስተኛና ጥቃቅን ንግድ ስራ በመሳተፍ የዕለት ገቢያቸውን እንዲያሻሽሉ ለማስቻል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ኃላፊው አስረድተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከሚካሄዱት ፕሮግራሞች አንዱ በሆነው የሰፈራ ፕሮግራም በአማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ህዝቦች ክልሎች ለአምስተኛ ጊዜ በጥናት ላይ የተመሰረተ ሰፈራ ለማካሄድ እንቅስቃሴ መጀመሩን አቶ ብርሃኑ አስታውቀዋል።

ሰፈራ በሚካሄድባቸው ክልሎች የመሬት ለምነታቸው ከተሟጠጠባቸው፣ የመሬት ጥበት ካለባቸውና ድርቅ በተደጋጋሚ ከሚያጠቃቸው አካባቢዎች የተውጣጡ 40 ሺ የሚሆኑ የቤተሰብ መሪ አርሶ አደሮችን የተሻለ ለምነት ወዳለቸው አዳዲስ ጣቢያዎች ለማስፈር ጥናት መጀመሩን ኃላፊው ገልፀዋል።

ሰፋሪዎቹ አምርተው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ ልዩ ልዩ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሲሆን፤ የተለያዩ የግብርና ምርት ግብአቶች አቅርቦትና የመሰረተ ልማት አውታሮችን ማስፋፋት ስራ እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።