|
ማህበሩ የስነተዋልዶ ጤናና ቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ለማጠናከርና የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ አደረገ |
አዲስ አበባ ጥቀምት 2/1999 /ዋኢማ/ የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች የስነተዋልዶ ጤናና ቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ለማጠናከርና ለማሻሻል የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡ፕሮጀክቱ ከፓካርድ ፋውንዴሽን ባገኘው 1 ሚሊዮን ዶላር ለሶስት አመታት የሚከናወን ነው፡፡ ፕሮጀክቱን በስነተዋልዶ ጤናና ቤተሰብ ምጣኔ ዙሪያ ለሚሰሩ አካላት ለማስተዋወቅ በደሳለኝ ሆቴል በተደረገ ውይይት ላይ የማህበሩ የቦርድ አባልና የፕሮጀክቱ የስራ አመራር ኮሜቴ ሊቀመንበር ዶክተር ምስጋናው ፋንታሁን እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች አማካኝነት የስነ ተዋልዶ ጤናና የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ለማጠናከር የሚያስችል ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በአማራ ክልል በሚገኙ የደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖች ለሶስት አመታት እንደሚከናወን አመልክተው፤ባለሙያዎች በስነተዋልዶ ጤናና በቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት አሰጣጥ ያለባቸውን ክፍተት ለመሙላት በዞንና በወረዳ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎችና ተቆጣጣሪዎች የተለያዩ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች፣የእውቀት ማጠናከሪያ መርጃ መሳሪያዎች አቅርቦት እንደሚከናወን አስረድተዋል። ፕሮጀክቱን ለማካሄድ የሚያስችል የመነሻ ጥናት በሁለቱም ዞኖች እንደሚከናወን የገለጹት ዶክተር ምስጋናው፤ከአማራ ክልል ጤና ቢሮና ከተለያዩ በስነተዋልዶ ጤናና በቤተሰብ ምጣኔ ዙሪያ ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የጤና አጠባበቅ ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር መንግስቱ አስናቀ በበኩላቸው በአገሪቱ የስነተዋልዶ አገልግሎት ፍላጎት እያደገ ቢመጣም ያለውን ሃብት በአግባቡ ለመጠቀምና የጤና ስርዓቱ አፈጻጸም ብቃት ማነስ በስነ ህዝብና በስነተዋልዶ ፕሮግራሞቹ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቱ ወቅታዊ እርምጃ ለመውሰድና የታለመውን ግብ ለማሳካት እንደሚያግዝ ተናግረዋል። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አስራት ገነት በበኩላቸው በክልሉ ሁለት ዞኖች የሚከናወነው ፕሮግራም በጤናው ዘርፍ የምዕተ አመቱን ግብ ለማሳካት ከተነደፉ ዋና አጀንዳዎች መካከል የስነተዋልዶ ጤናና የቤተሰብ ምጣኔ አገለግሎት ዋነኛው መሆኑን አስረድተዋል። ለግማሽ ቀን በተዘጋጀው ውይይት ላይ በስነተዋልዶ ጤናና ቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ዙሪያ የሚሰሩ የተለያዩ መንግሰታዊ ፣መንግሰታዊ ያልሆኑና ኛለም አቀፍ ድርጅቶች መገኘታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሸን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|