ፌዴራል ፖሊስ አገራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት ህብረ ብሄራዊ አደረጃጀቱን ማጠናከር እንደሚኖርበት ተጠቆመ

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/1999/ዋኢማ /የፌዴራል ፖሊስ ተቋማት በህግ የተጣለባቸውን አገራዊ ሀላፊነት በብቃት ለመወጣት እንዲችሉ ህብረ ብሄራዊ አደረጃጀታቸውን ማጠናከርና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሳሪያ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አንድ ምሁር ገለፁ።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅን 60ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ዛሬ በፌደራል ፖሊስ አዳራሽ በፖሊስ ከፍተኛ አመራር አካላት መካከል በተጀመረው ሲምፖዚየም ላይ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር አሰፋ ፍሰሃ ባቀረቡት ጥናታዊ ፁሁፍ እንደገለፁት፤የኢትዮጵያ ፖሊሶች በህመንግስቱ የተጣለባቸውን ሀላፊነት በብቃት ለመወጣት እንዲችሉ የአገሪቱን ህዝብ የሚወክሉበት፣ስልጠና የሚያገኙበትና፣የሃላፊነት ቦታን የሚጋሩበት ሁኔታን በማመቻቸት ህብረ ብሄራዊ አደረጃጀታቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል።

ቀደም ባሉት ስርዓቶች የፖሊስ ሀይል የተወሰነ ማህበረሰብን ብቻ የሚያገለግልና የአምባገነኖች የመጨቆኛ መሳሪያ እንደነበር ጠቁመው፤ የአሁኑ ፖሊስ ዋነኛ ተልዕኮ ግን ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን መጠበቅ እንደሆነ አስረድተዋል።

ፖሊስ የቀን ተቀን ስራውን ሲያካሄድ ታማኝነቱና ተገዥነቱ ለህገ መንግስቱ እንጂ ለሚደግፈው የፖለቲካ ፓርቲ ሊሆን አይችልም ያሉት ዶክተር አሰፋ ይህ ካልሆነ ወደሌላ የፖለቲካ ቀውስ ሊያስገባ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል።

የፖሊስ አባላት ከህዝቡ አመኔታና ከበሬታ እንዲኖራቸው ከተፈለገ ጡንቸኝነትን፣ ተደባዳቢነትንና ከህግ በላይ የሆነ አመለካከትን በማስወገድ ለህገ መንግስት መከበርና ተገዢ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ምሁሩ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ካለው የህዝብ ብዛት። የከፋ ድህነት እንዲሁም በከተሞች አካባቢ የተጨናነቀና ደረጃውን ያልጠበቀ መንደር መበራከቱ ወንጀል ለመፈፀም የተመቻቸ ቢሆንም በአንድ በኩል ሀይማኖታዊና ባህላዊ ምክንያቶች በሌላ በኩል የፖሊስ ሀይል በሚያደርገው ያልተቆጠበ ጥረት የተረጋጋ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

ከተለያዩ ክልሎችና ከፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራር አካላት የተሳተፉበት አገር አቀፍ ሲምፖዚየም ነገም ቀጥሎ እንደሚውል ከወጣው ፕሮግራም ለመረዳት መቻሉን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።