በጋንቤላ ክልል በግንዛቤ ማነስ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራሙን መተግበር እንዳልተቻለ ተገለጸ

ጋምቤላ ጥቅምት 2/1999/ዋኢማ / ፈጣንና ህዝባዊ አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ የተነደፈው የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራሙን ለመተግበር የክልሉ አመራር ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ የተፈለገውን ያህል ውጤት ሊመጣ እንዳልቻለ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አስታወቁ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ጓነር ሄር ዛሬ በጋምቤላ ከተማ በተዘጋጀው የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ሪፖርት የግንዛቤ ማስጨበጫ አውደ ጥናት ላይ እንደተናገሩት፤ባለፉት ዓመታት የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራሞች በክልሉ ፈጥነው ባለመተግበራቸው ምክንያት ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ሳይከናወን ቆይቷል።

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ማሻሻያ ፕሮግራም አካል ከሆኑት መካከል የበጀት ማሻሻያ ፕሮግራም በክልሉ እየተተገበረ ቢሆንም በሪመፎርሙ ዙሪያ የአመራሩ ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ የተፈለገውን ያህል ውጤት ሊመጣ እንዳልቻለ ገልፀዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራሙን በቀጣዩ ስራ ላይ ለማዋልና ሀብረተሰቡን በቀናነት ለማገልገል እንዲቻል የአስፈጻሚውን አካል ብቃት ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የክልሉ የአምስት ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር እስትራቴጂክ ዕቅድ መዘጋጀቱንና ስራ ላይ ለማዋል የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፤የልማት ዕቅዱን ህዝቡ በሚፈልገው መንገድ ለመተግበር የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራሙን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የክልሉ የወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ሪፎርም ፕሮግራም የስራ ክንውን አጠቃላይ መግለጫ እንዲሁም የበጀት ፣ የሂሳብ ፣የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት ፣የህግ ማዕቀፍ የውስጥ ኦዲትና የጥሬ ገንዘብ አስተዳደር ክፍያና የአሰራር ማሻሻያ ፕሮጀክቶች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው አውደ ጥናት ላይ የፌደራል ገንዝብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ማሞ ጊቶንና የፌዴራል ከፍተኛ ባለሙያዎችን ጨምሮ 189 የሚሆኑ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የአመራር አካላት መሳተፋቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።