ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካይነት ፈጣን የፍትህ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተገለፀ

መቀሌ ጥቅምት 2/1999/ዋኢማ/ የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍድ ቤት በቪድዮ ኮንፈረንስ አማካይነት ለህብረተሰቡ ፈጣን የፍትህ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገለፀ ።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና የፍድ ቤቶች የስቪል ሰርቪስ ማሻሻያ መምሪያ ኃላፊ አቶ ማሩ ኃይለሥላሴ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ከዚህ በፊት ከዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚቀርቡ የይግባኝ ጉዳዮች ለማየት ባለጉዳዮች ወደ መቀሌ መጓዝ የግድ ይል ስለነበር ከፍተኛ የገንዘብ ወጪና መንገላታት ይደርስባቸው ነበር።

ችግሩን ለመፍታት ባለፈው ዓመት የተዘዋዋሪ ችሎት አገልግሎት ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም ይህ አሰራር በማዕከል የስራ መጨናነቅ መፍጠሩንና ከፍተኛ የትራንስፖርትና የውሎአበል ወጪ መጠየቁን አቶ ማሩ አስረድተዋል።

እነዚህን ችግሮች ለማቃለልና ቀደም ሲል በይግባኝ ወደ መቀሌ ይመጡ የነበሩትን የፍትሐብሄርና የወንጀል ጉዳዮች ባለጉዳዮቹ ባሉበት የዞንና የወረዳ ከተሞች አፋጣኝ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት በፌደራል መንግስት ብቻ ይሰጥ የነበረው በቪድዮ ኮንፈረንስ የፍትህ አገልገሎት የመስጠት አሰራር ከትናንት ጀምሮ በመቀሌ ከተማ በተቋቋመው የቪድዮ ኮንፈረንስ ማዕከል አመካይነት ስራው ተጀምሯል።

ከትናንት ጀምሮ ሁመሩ ከተማ የቪዲዮ ኮንፈረንሱ የፍትህ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን የጀመረች ሲሆን አክሱም ሽሬ ማይጨው የዞን ከተሞችና አላማጣ፣ተንቤን፣ ውቅሮና ክልተአውላዕሎ ወረዳዎች በተያዘው ወር በቪዲዮ ኮንፈረንሱ የፍትህ አገልግሎት እንደሚያገኙ ገልፀዋል።

ከዞን ፍርድ ቤቶች ለሩቅ ወረዳዎች ይሰጥ የበረውን ተመሣሣይ የፍትህ አገልግሎት በየወረዳው ባሉት የፕላዝማ መሣሪያዎች አማካይነት ለመቀጠል ዕቅድ መያዙንም አስታውቀዋል ።

የቪዲዮ ኮንፈረንሱ መጀመር በተለይ ከሁመራና ከሌሎች ሩቅ ወረዳዎች በይግባኝ ወደ መቀሌ ለመምጣት ይታይ የነበረውን የትራንስፖርት ፣የአልጋ ፣የምግብና የምስክሮች ውሎ አበል ወጪዎችና ችግር ያስቀረዋል ተብሎ እንደሚታመን አስረድተዋል

ህብረተሰቡ በአቅራቢያው የፍትህ አገልግሎት ካገኘ ለመልካም አስተዳደር መሰፈን ፣ለልማትና ዲሞክራሲ መጠናከር አስተዋፅኦ እንዳለው አስገንዝበዋል።

እንደዚሁም ከሁለቱ ተዘዋዋሪ ችሎቶች ጋር የሚጓዙ ሬጂስትራሮችና የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ወደ አካባቢዎቹ በመሄድ ያጠፉት የነበረውን ጊዜና ገንዘብ ከመቆጠቡም በሻገር ባሉበት ሆነው ለህብረተሰቡ ፈጣንና ጥራት ያለው የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችላቸው ይታመናል ብለዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት ህብረተሰቡ ባቅራቢያው የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኝ ጠቅላይ ፍርድቤቱ ባደረጋቸው ሦስት ዘመቻዎች በይግባኝ ይመጡ የበሩትን 1ሺ 268 ጉዳዮች በአካባቢያቸው ዕልባት እንዲያገኙ ማድረጉን አቶ ማሩ አስረድተዋል።