የሉሜ - አዳማ ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን የአርሶ አደሩንና የሸማቹን ገበያ ለማረጋጋት በ16 ሚሊየን ብር የእህል ግዥ ጀመረ

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/1999/ዋኢማ/ በኦሮሚያ ክልል የሉሜ - አዳማ ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን የአርሶ አደሩንና የሸማቹን ገበያ ለማረጋጋት በመደበው 16 ሚሊየን ብር የእህል ግዥ መጀመሩን አስታወቀ። ባሁኑ ወቅት ለዓለም ገበያ የሚያቀርበው 80 ሺ ኩንታል ቦለቄ ግዥ በማካሄድ ላይ መሆኑን ገልጿል።

የዩኒየኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደመረ ደምሴ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ ዩኒየኑ የእህል ግብይቱን እያካሄደ ያለው በአርሶ አደሩ ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት ዋጋ መውረድ ችግርና በሸማቹ የሚታየውን የዋጋ ንረት ላማጣጣም ነው።

በዚህም በክልሉ ከፍተኛ የሰብል አምራች ከሆነው ምስራቅ ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች እስከ 65 ሺ ኩንታል የሚደርስ ሽምብራና ጤፍ በመግዛት የምግብ እህል ፍላጎት ጎልቶ ወደ ሚታይባቸው ከተሞችና ክልሎች ወስዶ ለመሸጥ መዘጋጀቱን አቶ ደመረ አስታውቀዋል።

እንዲሁም በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦለቄ አምራች በሆኑ አዳማ፣ ቦሰት፣ ሉሜ፣ ዱግዳ ቦራና አዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳዎች ዩኒየኑ በስድስት ሚሊየን ብር 80 ሺ ኩንታል ቦለቄ ገዝቶ ለአውሮፓና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ግዥ መጀመሩን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ የምርቱና የገበያ ተጠቃሚ እንዲሆን ሲባል ዩኒየኑ ከመቂ - ባቱ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን፣ ከኦሮሚያ ህብረት ሥራ ማስፋፊያና ከኦሮሚያ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮዎች፣ ከኦሮሚያ ገበያ ጥናት ኤጀንሲና ከአዋሽ መልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የግብይት ሥርዓትን ለማጠናከር በዞን ደረጃ በአስተዳደሩ የሚመራ አንድ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ የገበያና የግብይት ሥርዓት በማመቻቸት ላይ እንደሚገኝም አቶ ደመረ አመልክተዋል።

አርሶ አደሩ ለሃገር ውስጥም ሆነ ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራትና ደረጃቸውን በመጠበቅ ዩኒየኑ ግዥ ወደሚያካሄድባቸው ጣቢያዎች በማቅረብ ምርቱን በወቅቱ መሸጥ እንዳለበት ስራ አስኪያጁ ማሳሰባቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።