|
ሪጅኑ በ126 ሚሊየን ብር በሶስት ክልሎች የተለያየ የስልክ መስመር መዘርጋት ስራ እያከናወነ ነው |
አዳማ ጥቅምት 2/1999 ዋኢማ/ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የደቡብ ምሥራቅ ሪጅን ከ126 ሚሊየን ብር በላይ በጀት በሶስት ክልሎች የዲጅታል ቴሌፎን የማዞሪያ ኔት ወርክና የኦፕቲካል ፋይበር መስመር የመዘርጋት ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ። በኮርፖሬሽኑ የደቡብ ምሥራቅ ሪጅን ሥራ አስኪያጅ አቶ ተፈሪ ዘውዴ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ ከተያዘው አዲሱ በጀት ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ የመስመር መዘርጋት ተግባራት እየተከናወኑ ያሉት በገጠርና በከተሞች አካባቢ የስልክ አገልግሎት ሽፋን ባልተዳረሰባቸው በአፋር ፣አሮሚያና በአማራ ክልሎች ነው። ኮርፖሬሽኑ በመደበው ብር እየተከናወኑ ካሉት ሥራዎች መካከል በ14 ከተሞች የሙሉ አውቶማቲክ የዲጅታል ቴሌፎን ተከላ፣በ43 ከተሞች የማዞሪያና የኔት ወርክ ማስፋፋት ሥራ፣እንዲሁም ከሻሽመኔ እሰከ ጎባና ከአዳማ እስከ ጎባ ባለው መንገድ የኦፕቲካል ፋይበር የመዘርጋት ስራ እንደሚከናወን ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል። በተጨማሪም በስኩል ኔት የፕላዝማ ተጠቃሚ ያልሆኑ 48 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በቅርብ ቀን ውስጥ የፕላዝማ ተጠቃሚ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ ከመሆኑም በላይ ኔት ወርክ ሽፋን ኖሯቸው ስልክ ላላገኙ ለሁለት መቶ የገጠር ቀበሌዎችም ተጠቃሚ ለማድረግ ሥራ የተጀመረ መሆኑን አመልክተዋል። ኮርፖሬሽኑ ከዚህ በተጨማሪም ለቢሮና ለማዞሪያ አገልግሎት የሚውሉና ባለፈው ዓመት በሁለት ከተሞች የተጀመሩት የሁለት ሕንፃዎች ግንባታም በአሁኑ ጊዜ እየተፋጠነ በመሆኑ በዚህ ዓመት አጋማሽ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ አስረድተዋል። ሪጅኑ የአካባቢው ህብረተሰብ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም አገልግሎትን ለማዳረስ የተጠናከረ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።። ኋላቀር የገጠር ቀበሌዎችና በየከተሞቹ እየተዘረጉያሉትን የቴሌፎን መስመሮች አገልግሎት መስፋፋት ህብረተሰቡ ባለበት ሆኖ አስፈላጊውን መረጃ ለማግኘት እንደሚያስችለው ስራ አስኪያጁ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|