|
በጢያራ ከተማ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸው ተገለፀ |
መቀሌ ጥቅምት 2/1999/ዋኢማ/በዓፋር ክልል በራሕሌ ወረዳ በጢያራቦራ ከተማ ከ14 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የወረዳው አስተዳደር ገለፀ። የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ኡስማን ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ የክልሉና የጣሊያን መንግስታት፣እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ የተለያዩ የልማት ድርጅቶች በመደቡት ገንዘብ በርካታ ክፍሎች ያሉት የአስተዳደር ዘመናዊ ህንጻና የፍትህ ቢሮ ህንፃ ተገንብተዋል። እንደዚሁም አንድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ከሩቅ አካባቢ ለሚመጡ ተማሪዎች የመኖሪያ ቤቶች መገንባታቸውን ተናግረዋል። አንድ የውኃ ፕሮጀክት መገንባቱንና አንድ ትልቅ የኤሌክትሪክ ጀኔሬተር መተከሉን ጠቁመው፤ በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ዘመናዊ ጤና ጣቢያም በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ወደ ሆስፒታል ደረጃ ለማሳደግ ዕቅድ በመያዙ ህብረተሰቡ ወደ ተሻለ የህክምና አገልግሎት እንደሚሸጋገር አስረድተዋል ።
እንዲሁም ቀደም ሲል የነበረውን የስልክ አገልግሎት ወደ አውቶማቲክ ለመቀየር የሚያስችል ግንባታ በቅርቡ ከመጀመሩም በላይ በዘጠኝ ቀበሌዎች የሚኖሩ አርብቶ አደሮችንም በአቅራቢያቸው የሽቦ አልባ ስልክ ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል። በወረዳው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በከተማው በተገነቡት የተላያዩ ፕሮጀክቶች የከተማዋ ዕድገት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፤ከአምስት ሺ ያላነሱ የከተማው ነዋሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሆኑ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሸን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|