የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሶስተኛ ዘመን 2ኛ ዓመት ስራቸውን ዛሬ በይፋ ጀመሩ

አዲስ አበባ መስከረም 29/1999/ዋኢማ/ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በተያዘው ዓመት በሀገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ለማስፈንና ፈጣን ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ የሚያወጧቸውን ልዩ ልዩ አዋጆችንና ህጎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ፕሬዚደንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ አስገነዘቡ። የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሶስተኛ ዘመን 2ኛ ዓመት ስራቸውን ዛሬ በይፋ ጀምረዋል።

ፕሬዚደንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ምክር ቤቶቹን ስራ ለማስጀመር ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የስብሰባ አዳራሽ ተገኝተው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንዳስገነዘቡት፤ በምክር ቤቶቹ የሚወጡ ህጎችና አዋጆች የተፋጠነ ልማትንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚችሉ በአስፈፃሚ አካላትና በመላው ህብረተሰብ ርብርብ ተግባራዊ መሆን ሲችሉ ነው።

በዓመቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ የሚያፀድቃቸው አዋጆች ዴሞክራሲን ለማስፈንና መልካም አስተዳደርን ለመገንባት ቁልፍ ሚና ያላቸው እንደሚሆኑ ፕሬዚደንቱ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

ከነዚህም አዋጆች መካከል የሲቪል ሰርቪስ ፕሮግራሙን ለማጠናከር የሚረዳ የአስፈፃሚ አካላት የፕሬስና የብሮድ ካስት ኤጀንሲንና የማስታወቂያ ሚኒስቴርን አደረጃጀትና ተልዕኮ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጆች ለምክር ቤቱ ቀርበው ይጸድቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረወል።

እንዲሁም የምርጫ ቦርድ ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሚናና ኃላፊነት ለመለየት የሚያስችል አዋጅ፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች ፈቃድ አሰጣጥና የጥብቅና አዋጅ፣ በህገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ለሽብር ተግባር ማዋልን የሚከለክሉ አዋጆች ለውይይት ቀርበው በምክር ቤቱ ይፀደቃሉ ተብለው ከሚጠበቁት ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ፕሬዚደንት ግርማ አስታውቀዋል።

በኢኮኖሚው መስክም ላለፉት ዓመታት የተመዘገበውን ዕድገት ለማስቀጠል የሚረዱ የግብርና ምርቶች የግብይት ስርአት፣ የኳራንቲን ጣቢያዎች ማቋቋሚያ፣ አነስተኛ የገጠር ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማሻሻያና የተፋሰስ ሀብት ልማት አካላት ባለስልጣናትን ማደራጃ አዋጆች ምክር ቤቱ ተወያይቶ ያፀድቃቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

በከተሞች የሚታየውን የንፁህ መጠጥ ወኃ አቅርቦት ለማሻሻል የሚወጣ የወኃ ልማት ፈንድ ማቋቋሚያ ረቂቅና በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚገነቡ ህንፃዎች ማሟላት የሚገባቸውን ደረጃ ለመወሰን የሚያስችል ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅን ጨምሮ የመሬትና መሬት ነክ ንብረት አዋጅና የሴቶች ልማት ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጆችን ያጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

በተጨማሪም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማሻሻያ አዋጅና የመንግስት የ1999 በጀት ዓመት መደበኛና ካፒታል ስራዎች ማስፈፀሚያ የሚጠቀምበትን በጀት ተወያይቶ እንደሚያፀድቅ ገልጸዋል።

በምክር ቤቶቹ የሚወጡ እነዚሁ አዋጆች የተፋጠነ ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በመሆናቸው በየደረጃው የሚገኙ አስፈፃሚ አካላትና ህዝቡ በንቁ ተሳትፎ ተግባራዊ እንዲያደርጉም ፕሬዚደንቱ ጥሪ ማቅረባቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።