አፍሪካዊያን አካል ጉዳተኞች በሁሉም የስፖርት ዘርፎች እያደረጉት ያሉት ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ ተገለፀ

አዲሰ አበባ መስከረም 29/1999/ዋኢማ /አፍሪካዊያን የአካል ጉዳተኞች በአህጉራቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም የስፖርት ዘርፎች እያደረጉት ያለው ተሳትፎ እድገት እያሳየ መምጣቱን የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

የሚኒስቴሩ ተወካይ አቶ ጌታሁን ገብረ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ፓራ ሊምፒክ ኮሚቴ ድር ፋውንዴሽን እና ሬስፖ ከተባሉት የውጪ ሀገር መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የቤጅንግ ፓራ ሊሚፒክ ተሳትፎን በተመለከተ በምስራቅ አፍሪካ ለሚገኙ ሀገሮች ያዘጋጀቱን የምክክር አውደ ጥናት ዛሬ ሲከፍቱ እንደገለፁት፤ አፍሪካዊያን የአካል ጉዳተኞች በአፍሪካና በአለም አቀፍ ደረጃ በስፖርቱ ዘርፍ እያደረጉ ያሉት ተሳትፎ ከጊዜ ወደጊዜ እድገት እያሳየ መጥቷል።

በ2004 በአቴንስ በተካሄደ በፓራሊምፒክ ስፖርት ውድድር በርካታ አፍሪካዊያን መሳተፋቸውን ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስመዝገባቸውን ጠቁመው፤ይህ መሰል አውደጥናት በመስኩ ለሚደረገው ውድድር አጋዥ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፓራ ሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንትአቶ አበበ ገላጋይ በበኩላቸው አስር ያህል የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች የቤጅንግ ፓራሊሚፒክ ተሳትፎን በተመለከተ ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት ምክክርና የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ጠቁመው፤በአውድ ጥናቱ ላይ ከእያንዳንዱ ፓራ ሊምፒክ ኮሚቴ አባል ሀገራት ተወካዮች ሪፖርት እንደሚያቀርብም ገልፀዋል።

በረጅም ጊዜ ዕቅድ ከቤጅንግ አልፎ በለንደን ለሚደረገው ፓራ ሊምፒክ ውድድር ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚሰራ በመክፈቻው ላይ መገለፁን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።