|
የውሃ ሃብት በምግብ እህል እራስን ለማቻል ዋነኛ መሳሪያ መሆኑ ተገለፀ |
አርባ ምንጭ መስከረም 29/1999/ዋኢማ/ ድህነትን ለመቀነስና በምግብ እህል ራስን ለመቻል ጉልህ ድርሻ ያለውን የውሃ ሃብት ልማት ተኮር በሆኑ ዘዴዎች መጠቀም ተገቢ መሆኑን ተገለፀ። በዘላቂ የውሃ ዕድገትና አጠቃቀም ላይ የሚነጋገር አገር አቀፍ ሲንፖዚየም ዛሬ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተጀምሯል። በዩኒቨርስቲው ለ10ኛ ጊዜ እየተካሄደ ባለው ሲንፖዚየም የዩኒቨርስቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኢንጅነር ንጋቱ ጫፎ እንደገለጹት፤ ሃገሪቱ ያላትን ከፍተኛ መጠን ያለው የውሃ ሃብት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ በመስኖ ልማት፣ በሃይል ማመንጫና በቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ስራዎች ላይ መጠቀም ድህነትን ለማሰወገድ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአገሪቱ የተከናወኑ በርካታ የውሃ ልማት ፕሮጀክቶች በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የውሃ ሃብትን እንደ ዋነኛ የድህነት ማስወገጃ መሳሪያ ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት አስገንዝበዋል። በሲምፖዚየሙ 24 የምርምር ስራዎች እንደሚቀርቡ የተገለፀ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም በውሃ አጠቃቀምና አጠባበቅ፣ በመስኖ ልማት፣ በአፈር መሸርሸርና አጠባበቅ እንዲሁም በአየር ጸባይ ትንበያ ዙሪያ በቀረቡ የምርምር ስራዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ታውቋል። ውይይቱ በመስኖ ልማት ሂደት በሚያጋጥሙ የክትትል ማነስ ችግሮች፣ ድርቅ ስለሚበዛባቸው አካባቢዎች እንዲሁም ስለ ናይል ተፋሰስ ትኩረት የሚሰጥ ሲሆን፤ ከጎርፍ አደጋዎች ጋር ተያይዞም በአየር ፀባይ ትንበያ ላይ እንደሚነጋገር ከሲምፖዚየሙ አዘጋጆች ለመረዳት ተችሏል። በሲምፖዚየሙ ከምርምር ተቋማት፣ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችና ከውጭ አገራት የመጡ ከ150 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። በጀርመን መንግስት የምርምርና የስልጠና ዓቅም ፕሮጀክት ተወካይ ፕሮፌሰር ፎርች ጌርድም በክብር እንግድነት መገኘታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|