የሱማሌ ክልል ገቢ የመሰብሰብ አቅሙን ለማሳደግ የተለያዩ ስልቶች መቀየሱን አስታወቀ

ጅጅጋ መስከረም 29/1999/ዋኢማ /በሱማሌ ክልል በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘውን የገቢ አቅም ለማሳደግ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ገለፀ።ከገቢ አሰባሰብ ጋር በተያያዘ ህግ ወጥ ስራ በሚፈፅሙ ሰራተኞችና ተባባሪዎች ላይ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድም አስታወቋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዲ አህመድ ጋራድ እንደገለጹት በ1998 የበጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ ርእሶች 60 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ቢታቀድም የተሰበሰበው 52 ሚሊየን ብር ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

ለገቢው መቀነሰ ዋነኛ መንስኤ ህብረተሰቡ በታክስ አከፋፈል ላይ ያለው ግንዛቤ ማነስ ፤ በክልሉ በአንድንድ ዞኖች ተከስቶ በነበረው ድርቅ ምክንያት የንግድ ስራ በመቀዛዙ ነው ብለዋል ።

በቀጣዩ ዓመትም ከገቢ ግብር ፤ ካጫት ቀረፅ ፤ከመሬት መጠቀሚያና ፤ በክልሉ በስፋት ከሚገኘው የእንስሳት ሀብት ጨምሮ ከተለያዩ የገቢ ርዕሶች 60 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ በእቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ገልፀዋል።

ከገቢ አሰባሰብ ጋር የሚታዩ የአቅም ውስንነትና የተለያዩ ችግሮች ለማስወገድ ለሰራተኞች የተለየዩ ስልጠናዎች እንደሚሰጥ የተናገሩት አቶ አብዲ ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ አዳዲስ ምንጮችን ማጥናትና የታክስ ማሻሻያ ሪፎርም ፕሮግራምን ተግባራዊ በማድረግ ለውጥ ለማምጣት ርብርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በአንዳንድ ወረዳዎች በገቢ አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ህገ ወጥ አሰራሮችን ለማስወገድ የማስተማርና የተለያዩ ማስተካከያ እርምጃዎች ለመውሰድ ጥረት እነደሚደርግም የቢሮው ሀላፊ ገለፀዋል።

የክልሉ ርዕስ መስተዳደር አቶ አብዱላሂ ሀሰን በበኩላቸው የክልሉን ልማት ለማፋጠን ከፌዴራል በሚሰጥ በጀትና ድጎማ ብቻ ለውጥ ማምጣት ስለማይቻል ክልሉ ጠንካራ የገቢ ማሰባሰቢያ አቅም ሊኖረው ይገባል ብለዋል።

የገቢ ሰብሳቢ ቢሮዎች ከክልል እሰከ ወረዳ ከአቅም ውስንነት ባሻገር የአሰራርና የአስተዳደር ችግርም ጭምር ያለባቸው በመሆኑ ቢሮው ያቀደውን ገቢ መሰብሰብ እንዳልቻ አስረድተዋል።

የክልሉ የገቢ አቅም ለማሳደግ በቢሮ ውስጥ የሚታዩ የአሰራር ፤ የአስተዳደርና ከታክስ አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የጥገኝነት የሚከሰቱ ግድፈቶች ለማስተካከል ጥረት እንደሚደረግ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።

በተጨማሪ በገቢ ሰብሳቢ ቢሮዎች ብቃት ያላቸው ባለሞያዎችን ከመመደብ ጎን ለጎን የታክስ ማሻሻያ ፕሮግራሙን ስኬታማ ለማድረግ ለሰራተኞች ደግሞ የአጭርና የረጅም ጊዜ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ አቶ አብዱላሂ ማስታወቃቸውን የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘገባ ያመለክታል።