|
ማዕከሉ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሁለት የተሻሻሉ የቦሎቄ ዝርያዎችን በምርምር አገኘ |
አዋሳ መስከረም 29/1999/ዋኢማ/ የአረካ ግብርና ምርምር ማዕከል የአረሶ አደደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ሁለት አዳዲስና የተሻሻሉ የቦሌቄ ዝርያዎችን በምርምር ማግኘቱን አስታወቀ። የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ አግደው በቀለ ሰሞኑን በጋሞ ጎፋ ዞን ጎፋ ዙሪያ ወረዳ በቦርዳ ምርመር ጣቢያ በተካሄደ የመስክ ጉብኝት ላይ እንደገለፁት ማዕከሉ በምርመር ያገኛቸው አዲስና የተሻሻሉ ሁለት የቦሎቄ ዝርያዎች ኢባዶ እና ኦሞ 95 የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። እነዚሁ የቦሎቄ ዝርያዎች በሄከታር እስከ 30 ኩንታል ምርት የሚያስገኙ ሲሆን፣ ከምርምር ጣቢያዎች በተጨማሪ በአርሶ አደሮች ማሳ በተደረገ ሙከራ አጥጋቢ ውጤት መገኘቱንና በአረሶ አደሩም ዘንድ ተፈላጊነት ማግኘታቸውን ተናግረዋል። የቦሎቄ ዝርያዎቹ ለምግብነት የሚውሉ ከመሆናቸውም ባሻገር በገበያ ተፈላጊ በመሆናቸው የአርሶ አደሩን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብለዋል። የአርሶ አደሮችን ገቢ ለመጨመር እንዲቻልም የቦሎቄ አምራች አርሶ አደሮችን ምርት የሚቀበል ስታርች ኢንዱስትሪ ከተባለ የአገር ውስጥ ፋብሪካ ጋር ቅድመ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ገልፀዋል። ሰሞኑን በተካሄደው የመስክ ጉብኝት የተሳተፉ አርሶ አደሮችም ምርታማነትን ለማሳደግ የምርምር ማዕከሉ ለአርሶ አደሮች እያደረገ ያለውን ድጋፍ የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል ማሳሰባቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|