|
የአዋሽ ብሄራዊ ፓርክ በ9 ሺ 68 ቱሪስቶች ተጎበኘ |
አዲስ አበባ መስከረም 29/1999/ዋኢማ/ ባለፈው የበጀት ዓመት 9 ሺ 68 ቱሪስቶች የአዋሽ ብሄራዊ ፓርክ መጎብኘታቸውን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ከቱሪስቶች የሚገኘው ገቢም በዕጥፍ ጨምሯል። የፓርኩ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ አብዮት ኃይሌ "ቱሪዝም ያበለፅጋል" በሚል መሪ መፈክር የዓለም ቱሪዝም ቀን ትናንት በፓርኩና በመተሃራ ከተማ ሲከበር እንዳስታወቁት፤ ዓምና 5 ሺ 982 የሃገር ውስጥና 3 ሺ 86 የውጭ ሃገር ቱሪስቶች የፓርኩ ቤተ መዘክርን ጨምሮ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ የዱር እንስሳት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። ፓርኩን ከጎበኙት የውጭ ቱሪስቶች መካከል ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ስፔን፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ አውስትራሊያና የሆላንድ ቱሪስቶች በብዛት የሚገኙበት ሲሆን፤ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ሳላ፣ አጋዘን፣ አንበሳ፣ አምባራይሌና ሌሎች የዱር እንስሳት የገብኚዎች ቀልብ መሳባቸውን ተናግረዋል። በዚህም በበጀት ዓመቱ 175 ሺ 714 ብር ገቢ መገኘቱን ገልጸው፤ ፓርኩን የጎበኙት ቱሪስቶች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ3 ሺ 417 ገቢው ደግሞ በዕጥፍ መጨመሩን አቶ አብዮት አስታውቀዋል። በተያዘው የበጀት ዓመት ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ 946 ኢትዮጵያውያንና አንድ ሺ ሶስት የውጭ ቱርስቶች ፓርኩን በመጎብኘታቸው 58 ሺ 724 ብር ገቢ መገኘቱን ተወካዩ ተናግረዋል። ይሁንና በድርቅና በግጦሽ ሳር ፍለጋ ሳቢያ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች የፓርኩን ክልል ጥሰው በመግባት ቤት በመስራት፣ ከብቶቻቸውን ወደ ዱር እንስሳት መኖሪያ አካባቢዎች በመልቀቅ፣ አልፎ አልፎም የዱር እንስሳቱን በመግደል ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል። የምስራቅ ሸዋ ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሱልጣን ሁሴን በበኩላቸው የአዋሽ ብሄራዊ ፓርክን ጨምሮ በዞኑ ለቱሪዝም መስህብ የሆኑ የተለያዩ ፏፏቴዎች፣ ኃይቆች፣ ባህላዊ አልባሳት፣ የጦር መሳሪያዎችና ብርቅዬ የዱር እንስሳት እንዳሉ ጠቁመው፤ መስህቦቹ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተናግረዋል። በፓርኩ አካባቢ የሚነሱ ችግሮች ከህብረተሰቡ የግንዛቤ ማነስ የመነጩ በመሆናቸው ችግሩን ለመቅረፍ ለአካባቢው ህዝብ ስለፓርኩ ጠቀሜታ ትምህርት እንደሚሰጥ ገልጸዋል። የዞኑ አስተዳደር ተወካይ አቶ አብደላ ጎዳና ህዝቡ፣ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የክልልና የሃገር ሀብት ቅርስና መገለጫ የሆነውን የአዋሽ ብሄራዊ ፓርክን ጨምሮ ሌሎች የቱሪዝም መስህቦችን በመጠበቅና በመንከባከብ እንዲሁም ከአደጋ በመታደግ ጥቅም ላይ ለማዋልና ለትውልድ ለማስተላለፍ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። የመተሃራ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ የዞንና የወረዳ ባለስልጣናትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ፓርኩንና በመተሃራ ከተማ የተዘጋጀውን የስዕልና ፎቶግራፍ ኤግዚብሽን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። በ1961 ህጋዊ ዕውቅና ያገኘው የአዋሽ ብሄራዊ ፓርክ 756 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት፣ 81 ዝርያ ያላቸው አጥቢ የዱር እንስሳት፣ 453 የአዕዋፍ ዝርያዎችና ለምርምር የሚውሉ በርካታ የዕጽዋት ዝርያዎች እንዲሁም 51 የጥበቃ፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና ባለሙያዎች እንዳሉት በዕለቱ ከተደረገው ገለጻ መረዳት መቻሉን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|