የአርሶ አደሩን ባህላዊ ዕውቀቶች ለዘላቂ የግብርና ልማት እንደ ግብአት መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

አዲስ አበባ መስከረም 29/1999 /ዋኢማ / በየአካባቢው የሚገኙ የአርሶ አደሩን ባህላዊ ዕውቀቶች ለዘላቂ የግብርና ልማትና የመሬት አጠቃቀም ስትራቴጂ ስኬት እንደ ግብአት ለመጠቀም የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አስታወቁ።

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አህመድ ናስር ዛሬ በክርስቲያን የልማትና በጎአድራጎት ድርጅት አዳራሽ የተካሄደውን በመሬት ይዞታና አጠቃቀም ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት በንግግር ሲከፍቱ እንደገለጹት፤ የአርሶ አደሩ ነባርና ባህላዊ ዕውቀቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ ካለመዋላቸውም በላይ ተገቢው ትኩረት ስላልተሰጣቸውና ጥበቃ ስላልተደረገላቸው እየተዳከሙና እየጠፉ ናቸው።

የአርሶ አደሩ ባህላዊ ዕውቀቶች ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ ለመሬት አጠቃቀምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የወጡ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ የማድረግ ዓቅም ያላቸው በመሆኑ መጠናትና በቴክኒዎሎጂ ታግዘው ጥቅም ላይ መዋል ይኖርባቸዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዚህ ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በአመት እስከ 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ቶን አፈር በነፋስና በጎርፍ እየታጠበ እንደሆነና እስከ 200 ሺ ሄክታር የሚገመት የተፈጥሮ ደን እንደሚወድም አመልክተው፤ ይህንን ሀኔታ በመቀየርና የአፈር ለምነትን በመጠበቅ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በገበሬው ነባር ዕውቀት ላይ የተመሰረቱ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የዘላቂ መሬት አጠቃቀም ፎረም ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ኃብተማሪያም አባተ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በአውደ ጥናቱ ላይ የቀረቡት በደቡብ ክልል የወናጎ ወረዳ አርሶ አደሮች የእርሻና ደን ጥምር አመራረት፣ በአማራ የወደበ እየሱስና በኦሮሚያ የጫንጮ አቤ ቀበሌዎች የተበጣጠሰ የአርሶ አደርመሬት አጠቃቀም በአካባቢ ጥበቃና በምግብ ዋስትና ላይ ያለውን ተጽዕኖ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ያስገኙት ውጤትለሌሎች ተመሳሳይ ኤኮሎጂ ላላቸው አካባቢ አርሶ አደሮች ልምድ ሆነው እንዲያገለግሉ ይደረጋል።

እንዲሁም በአማራ ክልል የተካሄደውን የመሬት ምዝገባና የተሰጠው የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ አስመልክቶ የተጠናው ጥናትም ለሌሎች ክልሎች እንደ ተሞኩሮ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

ከክርስቲያን የልማትና ተራድኦ ድርጅትና ከኤስ ኦ ኤስ ሳህል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የዘላቂ መሬት አጠቃቀም ፎረም ባዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ እርሶ አደሮች፣ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች፤ ተመራማሪዎች መሳተፋቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።