|
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ለምርምር ስራዎች 500 ሺ ብር የሚደርስ በጀት መድቦ በመንቀሳቀስ ላይ ነው |
አርባ ምንጭ መስከረም29/1999/ዋኢማ/ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ በዘንድሮ ዓመት ለሚያካሂዳቸው 12 የምርምር ፕሮጀክቶች እስከ 500 ሺ ብር የሚደርስ በጀት መድቦ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን አስታወቀ። ዩኒቨርስቲው የምርምርና ሕትመት አገልግሎት አስተባባሪ ዶክተር መኮንን አያና ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በዩኒቨርስቲው ምሁራንና የተለያዩ አካላት የተቀረፁ 12 የምርምር ፕሮጀክቶች በሚቀጥሉት ሳምንታት ተግባር ላይ ይውላሉ። ፕሮጀክቶቹ የመንግስትን ፖሊሲና የህብረተሰቡን ፍላጐት ያገናዘቡ መሆናቸውን የገለጹት አስተባባሪው፤ ምርምሮቹ በውሃና ውሃ ነክ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በእርሻና ጥቃቅን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ትኩረት እንደሚሰጡ አስረድተዋል። በአገሪቱ የተለያዩ ፖሊሲ አውጪዎችና አስፈፃሚዎችን የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ዩኒቨርስቲው ባለፉት ዓመታት ከ4 ሺ 500 በላይ የምርምር ስራዎችን በመጽሄት መልክ ማሰራጨቱን ጠቁመው፤ በዚህም ዩኒቨርስቲው በምግብ እህል ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ተሳታፊ መሆኑን አመልክተዋል። ዩኒቨርስቲው ከዚህ ቀደም በውሃ ቴክኖሎጂነቱ ይታወቅ እንደነበር የገለፁት ዶክተር መኮንን፤ የውሃ ቴክኖሎጂውንና የተማሪዎች ቅበላ ዓቅሙን በ30 በመቶ እንደሚያሳድግ አስረድተዋል። በውሃው ዘርፍ የነበሩትን አራት የትምህርት ፕሮግራሞች ወደ ስድስት በማሳደግ በሚትሪዮሎጂ እንዲሁም ከውሃ አቅርቦትና ጥራት ጋር ተያያዥነት ባላቸው አዳዲስ የትምህርት ዘርፎች ዘንድሮ ስልጠና መስጠት እንደሚጀምር አስታውቀዋል። |
|
|
|
|