በወረዳው በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ የተሰማሩ ወገኖች 7ሺ ለሚጠጉ ወገኖች የስራ እድል መፍጠራቸው ተገለጸ

አክሱም መስከረም 29/1999 /ዋኢማ/ በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በሽሬ እንዳስላሴ ወረዳ በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ የተሰማሩ ወገኖች 7ሺ ለሚጠጉ ነዋሪዎች የስራ እድል መፍጠራቸውን የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ።ተቋማቱ ለእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ አጋዥ የሆኑ የተለያዩ የእርሻ መሳሪያዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆናቸው ተገልጿል።

የሽሬ እንዳስላሴ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የማስታወቂያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብራሃለይ አበራ ሰሞኑን እንዳስታወቁት በወረዳው ሦስት ቀበሌዎች 4ሺ 822 ሰዎችበተለያዩ የጥቃቅንና የአነስተኛ ንግድ ድርጅቶች ተሰማርተዋል።

ባገኙት ከ9 ሚሊየን ብር በላይ ብድርአነስተኛ ድርጅቶችን አቋቁመው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉት እነዚህ ወገኖች ለ6ሺ 922 ስራአጦች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠራቸውንም ተናግረዋል።

እነዚህ በተሰጣቸው ብድር ለነዋሪዎቹ የስራ እድል ከፈጠሩት መካከል 3ሺ 79 በአገልግሎት ሰጪነት ፣ 1ሺ 425 በኮንስትራክሽን እና 318 በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ መሆናቸውንም አቶ አብራሃለይ አስረድተዋል።

በተለይ በኢንዱሰትሪው ዘርፍ የተሰማሩት ለእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ አጋዥ የሆኑ የተለያዩ የእርሻ መሳሪያዎች እና ቀላል ቴክኖሎጂዎች በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶአደሩ እያቀረቡ መሆናቸውን ሃላፊው ተናግረዋል።

በተቋማቱ እየቀረቡ ካሉት የእርሻ ቴክኖሎጂዎች መካከል ለመስኖ አገልልግሎት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ትሪድል ፓምፖች ፣ ለዘመናዊ የንብ እርባታ ስራ የሚያገለግሉ ዘመናዊ የንብ ቆፎዎች እና የተለያዩ መሳሪያዎች እንደሚገኙባቸውና ባለፈው ዓመት ብቻ በእነዚህ ድርጅቶች በድምሩ ከ12ሺ 800 በላይ የተለያዩ የእርሻ መሳሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች ወደ አርሶአደሩ አንዲገቡ መደረጉን አስረድተዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ወገኖች በአሁኑ ጊዜ የካፒታል መጠናቸውን በማሳደግ የወሰዱትን ብድር መመለስ መጀመራቸውን ሃላፊው መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።