ድርጅቱ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለው እንቅስቃሴ መጀመሩን ገለጸ

አዲስ አበባ መስከረም 29/1999/ዋኢማ/ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት መሰረታዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ለውጥ ለማምጣት ባካሄደው ጥናት መሰረት በተያዘው የበጀት ዓመት አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታወቀ። የዘንድሮው የዓለም ፖስታ ቀን “በደንበኞች መታመንን ለማትረፍ ጥራት ያለውን አገልግሎት በሙሉዕነት ማቅረብ” በሚል መርህ ዛሬ ለ35ኛ ጊዜ ተከብሮ መዋሉንም ገለፀ።

የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት አገልግሎት ኃላፊ አቶ እሸቱ ገለቱ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ ድርጅቱ በሚሰጣቸው መደበኛ አገልግሎቶች ላይ መሰረታዊ የአሰራር ለውጥ ለማምጣት የሚያስቸሉ ጥናቶች ተካሂደዋል።

በዚህም መሰረት በተያዘው የበጀት ዓመት ድርጅቱን የዘመናዊ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ ለደንበኞች ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀዋል።

ከተደረጉት ማሻሻያዎች ውስጥ የደንበኞች ሳጥን ጉብኝት እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ የማራዘም፣ መልዕክቶችን በራስ ትራንስፖርት በመጠቀም ለደንበኞች የማስተላለፍ አሰራሮች ተሞክረው አበረታች ውጤት እንደተገኘባቸው ተናግረዋል።

እንዲሁም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በተመረጡ ስምንት ፖስታ ቤቶች የፖስታ ገንዘብ ቁጠባ አገልግሎት ለመጀመርና በጉምሩክ ባለስልጣን የሚላኩ መልዕክቶችን በውክልና ተረክቦ ለመስራት ዝግጅት መደረጉን አቶ እሸቱ ገልጸው፤ በድርጅቱ የሚሰጡ የደብዳቤዎችና ጥቅል መልዕክቶች፣ የሐዋላና የፈጣን መልዕክት ነባር አገልግሎቶችን ለደንበኞቸ በአንድ መስኮት ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ከአገልግሎት ማሻሻያዎቹ በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ 17 ሺ 700 የግል የፖስታ ሳጥኖች ተከላ፣ 12 ወኪል የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን ወደ መደበኛ የማሳደግ፣ 125 አዳዲስ የመልዕክት ጣቢያዎችን ለመክፈት መታቀዱንም አመልክተዋል።

የመልዕክቶች ደህንነት ለማስጠበቅም ፖስታ ሲዘረዘርና ወደ ሳጥኖች ገቢ ሲደረግ በቪዲዮ ካሜራ የተደገፈ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አቶ እሸቱ ገልጸው፤ በዚህም ከደንበኞች የሚመጡ ቅሬታዎች እየቀነሱ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዘንድሮው የዓለም የፖስታ ቀን “በደንበኞች መታመንን ለማትረፍ ጥራት ያለውን አገልግሎት በሙሉዕነት ማቅረብ” በሚል መርህ ዛሬ በሀገራችን ለ35ኛ ጊዜ ተከብሮ መዋሉን ኃላፊው አስታውቀዋል።

በዓሉ በደብዳቤ አጻጻፍ ለቀረቡ ተወዳዳሪዎች ሽልማት በመስጠት፣ በሙዚቃ ፌስቲቫል፣ በፖስታ ሙዚየም ጉብኝትና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሮ መዋሉ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በ1886 በሚኒሊክ ዘመነ መንግስት የተመሰረተ ሲሆን፤ አገልግሎቱን ለማሻሻል በ1958 በወጣው አዋጅ ራሱን ችሎ በአዲስ መልክ መቋቋሙን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።