በክልሉ ህዝቡን የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ ለማድረግ አስፈፃሚ አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ተገለጸ

ባህርዳር መስከረም 28/1999/ዋኢማ/ በአማራ ክልል ዴሞክራሲን፣ የመልካም አስተዳደርንና ሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን በሁሉም የመንግስት እርከኖች ተግባራዊ ለማድረግ አስፈፃሚ አካላት ከመቼውም ይበልጥ ሊረባረቡ እንደሚገባ የክልሉ ዓቅም ግንባታ ቢሮ አሳሰበ።

በባህርዳር ከተማ የስራ አመራር ኢንስቲቲዩት ለሶስት ሳምንታት የሰለጠኑ ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ የተውጣጡ የአቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊዎች ትናንት ስልጠናውን ሲያጠናቅቁ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ስማቸው ንጋቱ እንዳሳሰቡት፤ በክልሉ መሰረታዊ ችግር ሆኖ የቆየውን የማስፈፀም ዓቅም ማነስ ችግርን ለመፍታት በየደረጃዎች የሚገኙ አስፈፃሚ አካላት ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል።

የመልካም አስተዳደር፣ ዴሞክራሲና ሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ የሚቻለው አስፈፃሚ አካላት ሕዝብን አሳምኖ የመስራት ዓቅም ሲኖራቸው መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ለተግባራዊነቱም ሕብረተሰቡ የስልጣን ባለቤትነት መብቱን የሚያረጋገጥበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

እንዲሁም ሕብረተሰቡ ከመንግስት የሚፈልገውን አገልግሎት በተሟላና ፈጣን በሆነ መንገድ እንዲያገኝ አስፈፃሚ አካላት የጋራ አመራር ጥበብን በመጠቀም ሚዛናዊ የሆነ አሰራርን ማስፈን እንደሚገባቸው ምክትል አስገንዝበዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የስራ አስፈፃሚ አካላት የባለጉዳዮችን ቅሬታ የሚቀበል ባለሙያ በመመደብ ሕዝቡ የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሰራር መዘርጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የአማራ ክልል የስራ አመራር ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ አንባው በበኩላቸው ኃላፊዎቹ በስልጠና ቆይታቸው በለውጥ ስራ አመራር፣ በስትራቴጅክ ዕቅድ፣ በስራ አፈፃፀም፣ በጊዜ አጠቃቀምና ስራን እንደገና ማደራጀት ላይ ያተኮረ ትምህርት መቅሰማቸውን ተናግረዋል።

በስልጠናው 349 የሚሆኑ የክልል የዞንና የወረዳ የስራ አስፈፃሚ አካላት በሶስት ዙር መካፈላቸውንናከነዚህም ውስጥ 22ቱ ሴቶች መሆናቸውን አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል።

ስልጠናው የክልሉ ዓቅም ግንባታ ቢሮ ከአማራ ክልል ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑንም ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።