|
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለዘላቂ የውሃ ዕድገትና አጠቃቀም የሚያግዙ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑ ተገለጸ |
አርባምንጭ መስከረም 28/1999/ዋኢማ/ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለአገሪቱ ዘላቂ የውሃ ዕድገትና አጠቃቀም የሚያግዙ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን ገለፀ። ዩኒቨርሲቲው ዘላቂ የውሃ ዕድገትና አጠቃቀም በሚል ርዕስ ነገ ሃገር አቀፍ ሲምፖዚየም ያካሂዳል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ህትመት አስተባባሪ ዶክተር መኮንን አያና ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ የዩኒቨርሲቲው መምህራን በውሃ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ምርምሮችን እያካሄዱ ነው። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 16 የምርምር ውጤቶች መቅረባቸውን አስተባባሪው ገልጸው፤ በአባያና ጫሞ ሃይቆች እንዲሁም በናይል ተፋሰስ ዙሪያ ለሚደረጉ ውይይቶች የሚረዱ ጠቃሚ ሃሳቦች ለተለያዩ አካላት መሰጠታቸውን ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው የመስኖ አጠቃቀምና የምርት ዕድገት ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱንም ገልጸዋል።
በአርሶ አደሩ ማሳ የሰርቶ ማሳያ ስራዎችን የማከናወንና አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱን ዶክተር መኮንን አስታወቀዋል።
ዩኒቨርስቲው ''ዘላቂ የውሃ ዕድገትና አጠቃቀም'' በሚል ርዕስ ነገ ለ10ኛ ጊዜ ሃገር አቀፍ ሲምፖዚየም እንደሚያካሂድም አስተባባሪው አስረድተዋል። ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ሲምፖዚየም አዳዲስ የውሃ ቴክኖሎጂዎች እንደሚተዋወቁና በሃገር ውስጥና ውጭ ሀገራት ምሁራን የተዘጋጁ ጥናታዊ ፅሁፎች እንደሚቀርቡ አስረድተዋል። |
|
|
|
|