የሐረማያ ዩኒቨርስቲ ለምግብ ዋስትና ዕገዛ የሚያደርጉ 126 የምርምር ፕሮጀክቶች በማካሔድ ላይ ነው

ሐረር መስከረም 28/1999/ዋኢማ/ የሐረማያ ዩኒቨርስቲ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ለምግብ ዋስትና ዕገዛ የሚያደርጉ 126 ነባርና አዲስ የምርምርና ጥናት ፕሮጀክቶችን በማካሔድ ላይ መሆኑን አስታወቀ።

የዩኒቨርስቲው ምርምርና ስርፀት ዳይሬክተር ዶክተር ታደለ ተፈራ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ዩኒቨርስቲው የምርምርና ጥናት ፕሮጀክቶቹን በማካሔድ ላይ ያለው በዋናው ግቢና በሥሩ በሚገኙ ሰባት ንዑስ የምርምር ጣቢያዎች ውስጥ ነው።

የምርምር ፕሮጀክቶቹ በአዝዕርት ልማት፣ እንስሳት ዕርባታ፣ ማህበራዊ ምጣኔ ሀብት፣ ምግብ ሳይንስና ድህረ ምርት ቴክኖሎጂ የምርምር ዘርፎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ዶክተር ታደለ ገልፀዋል።

የአርሶ አደሩን ባህላዊ አሰራር ዘመናዊ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲያስችሉ በአዝርዕት ልማት ዘርፍ ምርምር እየተደረገባቸው ከሚገኙት ፕሮጀክቶች መካከል የማሽላ፣ በቆሎ፣ ለውዝ፣ ድንች፣ ጥራጥሬ፣ ስንዴ፣ ሥራ ሥር፣ አትክልትና ፍራፍሬ ሰብሎች ይገኙበታል።

በእንስሳት ዕርባታም እንዲሁ የእንስሳት ሥርዓተ አመጋገብ፣ የእንስሳት ጤና ምርምር፣ የግመል፣ በግና ፍየል፣ የንብ፣ የዶሮ፣ የሥጋና የወተት ከብቶች ምርታማነት ማሻሻያዎች ምርምር እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።

በዋናው ግቢ፣ በድሬዳዋ፣ ባቢሌ፣ ጅጅጋ፣ መልካ ጀብዱ፣ ሂርና፣ ጎሮ ሙጢና ፈዲስ በሚገኙ ንዑስ የምርምር ጣቢያዎች አማካኝነት የሚካሔዱት እነዚሁ ምርምሮች ሲጠናቀቁ የተሻለ የሥጋና የወተት ምርት የሚሰጡ ዝርያዎች እንደሚያስገኙ ዶክተር ታደለ አመልክተዋል።

ዩኒቨርስቲው የምርምር ፕሮጀክቶቹ ፍፃሜ እንዲያገኙ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ድርጅትም የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።