ከቀረጥ ነጻ ገብተው ወደ ሦስተኛ ወገን የተላለፉ ተሽከርካሪዎችን ሕጋዊ የማድረጊያው የጊዜ ገደብ ተራዘመ

አዲስ አበባ, ጥቅምት 25 ቀን 1999 - የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን ከቀረጥ ነጻ ገብተው ወደ ሦስተኛ ወገን የተላለፉ ተሽከርካሪዎችን ሕጋዊ ለማድረግ የተላለፈውን የጊዜ ገደብ አራዘመ፡፡ የሕገወጥ ዕቃዎች አሻሻጥ፣ አያያዝና የወረታ ክፍያዎችን ለመወሰን የሚያስችል መመሪያ ወጥቷል፡፡

ባለሥልጣኑ ትናንት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ የገቡና ከገቡ በኋላ በሕገ ወጥ መንገድ የቀረጥ ነፃ መብት ለሌላቸው ግለሰቦች ተላልፈው የሚገኙ ተሽከርካሪዎች አስፈላጊውን ቀረጥና ታክስ እንዲከፍሉ በተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጉን ገልጿል፡፡ በጥሪው መሰረት እስካሁን በርካታ የተሽከርካሪ ባለቤቶች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የጉምሩክ ጣቢያዎች እየቀረቡ በፈፀሙት የቀረጥና ታክስ ክፍያ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን አስታውቋ፡፡

 ባለሥልጣኑ ቀደም ሲል ባስተላለፈው ጥሪ መሰረት የስም የማዘዋወር ማብቂያ ጊዜ እስከ መስከረም 30 ቀን 1999 ዓ.ም እንደነበር አመልክቶ፣ ሆኖም አሁንም በርከት ያሉ ግለሰቦች በተደራጀ መልኩ የጊዜ ገደቡ እንዲራዘምላቸው አቤቱታ በማቅረባቸው ቀደም ሲል በተገለጸው መሰረት የቀረጥና ታክሱን አምስት በመቶ ተጨማሪ ክፍያ እየከፈሉ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 1999 ዓ.ም ድረስ በማራዘም የሚያስተናግድ መሆኑን ገልጿል፡፡

በተጨማሪም የገቢዎች ሚኒስቴር ከቀረጥ ነጻ ገብተው ለሦስተኛ ወገን የተላለፉ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሕጋዊ መስመር ለማስገባት እያደረገ ያለው የተጠናከረ እንቅስቃሴ አንዱ አካል የሆነውን የሕገ ወጥ ዕቃዎች አሻሻጥ፣ አያያዝና የወረታ ክፍያዎች ለመወሰን የሚያስችል መመሪያ እንዳወጣም አስታውቋ፡፡  

መመሪያው ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ ገብተው በሕገ ወጥ መንገድ ለሦስተኛ ወገን የተላለፉ ተሽከርካሪዎችን ሕግና ሥርዓት በማስያዝ ረገድ መላውን የኅብረተሰብ ክፍል በሚያሳትፍ መንገድ ለመፈፀም በሚያስችል መንገድ የተቀረፀ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

ባለሥልጣኑ በሕገ-ወጥ መንገድ ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው የሚገኙ ተሽከርካሪዎችን በበቂ መረጃ አስደግፈው ለጠቆሙ ግለሰቦች 15 በመቶ ወሮታ የሚከፍል ሲሆን፤ ለያዥ ድጋፍና ትብብር ለሚያደርግ ወገን ደግሞ በተመሳሳይ አምስት በመቶ ወሮታ እንደሚከፍል ገልጿል፡፡ ከቀረጥ ነፃ ባለመብት ውጪ ሆኖ የተገኘው ዕቃ የተያዘው ከባለሥልጣኑ ሠራተኞች ተሳትፎ ውጪ በክልል መስተዳድር አካላት ወይም በትራፊክ ፖሊስ አባላት አሊያም በፌዴራል ፖሊስ አካላትና በመከላከያ ሠራዊት አባላት ከሆነ እንደተቋቋመ 25 በመቶ የወሮታ ክፍያ እንደሚከፈል አመልክቷል፡፡

ይህንን ለማስተናገድ የሚያስችል አደረጃጀትም ተጠናክሮ እንዲሠራ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን አስታውቋ፡፡  እስካሁን ድረስ በጊዜ ገደቡ ተጠቅመው በስማቸው ያላዞሩ የተሽከርካሪ ባለቤቶችም የጊዜ ገደቡ ከመድረሱ ከጥቅምት 30 ቀን 1999 ዓ.ም በፊት ሕጋዊ እንዲያደርጉና ኅብረተሰቡም ይህን አውቆ ከፌዴራል፣ ከክልል ሕግ አስከባሪ አካላትና ከጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት ሥርዓት በማስያዝ ረገድ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ባለሥልጣኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ኢዜአ