|
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረችው እንቀስቃሴ ፈጣን ዕድገት ለማምጣት እንደሚረዳት ተገለጸ |
ባህርዳር መስከረም 25/1999/ዋኢማ/ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረችው እንቀስቃሴ በሀገሪቱ ፈጣን ዕድገት ለማምጣት ከነደፈችው የዕድገት መርሃ ግብር እንደ አንድ አጀንዳ ከተወስደው ይበልጥ ተጠቃሚ እንደምትሆን የአሜሪካን ኤምባሲ የልዑካን ቡድን ገለጸ። ሀገሪቱ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል እንደትሆን ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት የወጪ ንግድ ስርዓቷን የሚያሳይ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገልጿል። የዓለም ንግድ ድርጅትን ህገና መርሀ ለማስተዋወቅ በባህርዳር ከተማ በተዘጋጀው ዓውድ ጥናት ላይ የተገኙት በአሜሪካን ኤምባሲ የልዑካን ቡድን ምክትል የቡድን መሪ ሚስ ጃኔት ዊልገስ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ጉዳይን እንደ አንድ የዕድገት መርሀ ግብር ልትመለከተው ይገባል። በተለይ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ብትሆን ህዝቧን በየደረጃው ተጠቃሚ ለማድረግ የዘረጋችው የዕድገት መርሃ ግብር የምጣኔ ሀብት ዕድገቷንና የውጪ ንግድ ስርዓቷን በማፋጠን በጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳካት እንደሚያስችላት ሚስ ዊልገስ ተናግረዋል። ሀገሪቱ የድርጅቱ አባል መሆኗ ከአሁን በፊት በስፋት ከምትታወቅባቸው የስጋና የቡና የወጪ ንግዶች በተጨማሪ በሌሎቹ አዳዲስ የንግድ መስኮች እንድትሰማራ ዕድል ይከፍትላታል ያሉት የቡድን መሪዋ፤ ለዚህም ድርጅቱ ህግና መርህን መሰረት አድርጎ ከለላ እንደሚሰጣት አስረድተዋል። ሀገሪቱ ድህነትን ለመቀነስ እንደ አንድ አማራጭ በምትጠቀምበት የኢንቨስትመንት መስክ ቢሆንም በተለያዩ ዘርፎች የሚሰማሩ ባለሀብቶች አስተማማኝ ዋስትና እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ለምታደርገው እንቅስቃሴ የአሜሪካን መንግስት ድጋፍ እንደማይለያት አመልክተው፤ የጀመረችው የአባልነት ሂደት እንቅስቃሴ ዘላቂ ልማቷን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ልትሰጠው እንደሚገባ ገልፀዋል። በዓውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት በፌደራል ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ አህመድ ቱሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን ከሶስት ዓመት በፊት ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ የውጪ ንግድ ስርዓቷን የሚያሳይ ሰነድ ማዘጋጀቷን ገልፀዋል። ሰነዱ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ወር መቅረቡን ያመለከቱት አቶ አህመድ፤ አንዳንድ ማስተካከያዎች ተደርገውለት ለዓለም የንግድ ድርጅት ፅህፈት ቤት የሚላክ መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በዓለም የንግድ ድርጅት አባል በመሆን አስተማማኝና ዘላቂ የወጪ ንግድ ዕድል እንድታገኝ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ስለ ድርጅቱ ህግና ደንቦች በቂ ግንዛቤ በመያዝ ለተግባራዊነቱ ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የክልሉ ርዕስ መስተዳደር አቶ አያሌው ጎበዜ በበኩላቸው ሀገሪቱ ዘላቂ ልማትን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ነድፋ በምትንቀሳቀስበት ወቅት የአባልነት ሂደቱን ለማፋጠን የሚካሄደው ጥረት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው መሆኑን ገልፀዋል። በዓለም የንግድ ድርጅት ውስጥ ያሉ ህጎችና ደንቦች በአግባቡ መተግበር የአሰራር ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲኖር ከማገዛቸውም በላይ ፈጣን ልማት እንዲመዘገብ ስለሚረዱ የአማራ ክልል ህዝብና መንግስት ለተግባራዊነቱ የላቀ ተሳትፎ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። ለሁለት ቀን በሚቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ዓውደ ጥናት ላይ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከትምህርት ተቋማትና ሲቪል ማህበራት የተወጣጡ ከ100 በላይ ሰዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|