|
የምዕተ ዓመቱን ግብ ለማሳካትና ድህነትን ለማጥፋት ለከርሰ ምድር ውሃ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተገለጸ |
| አዲስ አበባ መስከረም 25/1/1999/ዋኢማ/ የምዕተ ዓመቱን ግብ ለማሳካትና ድህነትን ለማጥፋት ሀገሪቱ ያላትን የከርሰ ምድር ውሃ ክምችት ለተለያዩ ግልጋሎቶች የሚውልበት መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባ የውሃ ሃብት ልማት ሚኒስትር አስገነዘቡ። መንግስት ብሔራዊ የውሃ ፖሊሲ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የከርስ ምድር ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ በቀረበ ጥናት ላይ የሚመክር ኮንፈረንስ ዛሬ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ሲጀመር ሚኒስትሩ አቶ አስፋው ዲንጋሞ እንዳስገነዘቡት፤ በሀገሪቱ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ በዘላቂነት ለማስወገድና በምግብ ራስን ለመቻል የከርሰ ምድር ውሃን ለልማት ማዋል ይገባል። ለዚህም ሀገሪቱ ያላትን የከርሰ ምድር ውሃ ክምችት መጠንን በጥልቅት መርምሮ በማወቅ ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድ መመቻቸት እንዳለበት ተናግረዋል። በዚህ ረገድ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ባለሞያዎች ዕገዛ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ በበኩላቸው እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ2000 የኢትዮጵያ የከርሰ ምደር ውሃ ሀብት ግምገማ ፕሮግራም ዕቅድ በኢትዮጵያ መንግስት መዘጋጀቱን አስታውሰው፤ በአገሪቱ የሚገኘው የከርሰ ምድር ውሃ ክምችት መጠንና ይህንኑን የሚያሳይ ካርታ እንደሚዘጋጅ አስረድተዋል። ፕሮግራሙ ሀገሪቱ በውሃ ሀብት መስከ ለማስመዝገብ ያቀደችውን ዕቅድ ለማሳካት የተዘጋጀ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የውሃ ሀብት እንዳላትና የኢኮኖሚ መሰረቷም ግብርና መሆኑን አቶ አለማየሁ ጠቅሰው፤ የውሀ ሀብቱን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል መጠነ ሰፊ ጥናትና ምርምሮች ተደርገው በጥቅም ላይ ማዋል እንዲቻል ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው የበኩሉን እንደሚያደርግ ተናግረዋል። የዩኒሴፍ ተወካይ ሚስተር ሐንስ እስፕሩት በበኩላቸው ድርጅታቸው ለፕሮግራሙ ማስፈፀሚያ የአንድ ሚሊየን ዶላር ዕርዳታ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። ድርጅታቸው ከእናቶችና ከህፃናት ጤና ጋር በተያያዘ የንፁህ ውሃ አቅርቦት በየአካባቢው ለማስፋፋት ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን ለመተግበር ያወጣውን ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ ዕገዛውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀዋል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ኮንፈረንስ ላይ ከዓለም አቀፍ ዩኒቨርስቲዎች፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ አካላት፣ ከዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ የተወከሉና ከሀገር ውስጥም የመንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች መሳተፋቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|