የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ሲራጅ ፌጌሳ በስዋዚላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሞት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ

አዲስ አበባ መስከረም 25/1999/ዋኢማ/ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ሲራጅ ፌጌሳ በስዋዚላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አልበርት ሂሻኔ ሻባንጉ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገለጹ። ለስዋዚላንድ ህዝብና ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ተመኝተዋል።

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሳ የስዋዚላንድ ኤምባሲ ባዘጋጀው የሃዘን መግለጫ መዝገብ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንገተኛ ሞት ጥልቅ ሐዘን የተሰማቸው መሆኑን በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስትና በራሳቸው ስም ገልጸዋል።

ለስዋዚላንድ ህዝብና ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን በመመኘት በሁለቱ አገራት መካከል ያለው መልካም ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አልበርት ሻባንጉ በህይወት ዘመናቸው የዋኔ ብሄራዊ የነጻነት ኮንግረስ የወጣቶች ክንፍ አባል፣ የአገሪቱ ብሄራዊ የመምህራን ማህበር ሊቀመንበር፣ የካቢኔ ሚኒስትርና በመጨረሻም የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ማገልገላቸውን ከስዋዚላንድ ኤምባሲ የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ሚስተር አልበርት የድሆችን ችግሮች ለመፍታት ቀድመው የሚገኙና የሴቶችን ጉዳይ በሚመለከት ለሚነሱ ጉዳዮች አቢይ ተልዕኮ በመውሰድ የሚንቀሳቀሱ ጠንካራና ተወዳጅ ሰው እንደነበሩም ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አልበርት ሂሻኔ ሻባንጉ ከ15 ቀናት በፊት በእርሻ ማሳቸው ውስጥ በድንገት ራሳቸውን በመሳታቸው ሆስፒታል እንደደረሱ በ67 ዓመታቸው ህይወታቸው ማለፉን የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘገባ አመልክቷል።