|
በሃገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በቤተሙከራ ዕገዛ የተወለደች ህጻን በመልካም ጤንነት ላይ እንደምትገኝ ተገለጸ |
አዲስአበባ መስከረም 25/1999/ዋኢማ/ በተለያየ ምክንያት መውለድ ያልቻሉ ባለትዳሮችን በህክምና ዕርዳታ እንዲወልዱ ለማስቻል በሃገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው ሙከራ በተያዘው ወር የመጀመሪያ ሳምንት የተወለደች ህጻን በመልካም ጤንነት ላይ እንደምትገኝ የቤተል ቲቺንግ ሆስፒታል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አስታወቁ። የህጻኗ እናትም ልጅ ለማግኘት እየፈለጉ መውለድ ያልቻሉ ቤተሰቦች ህክምናውን ቢሞክሩት ምኞታቸው ሊሳካላቸው እንደሚችል መክረዋል። የሆስፒታሉ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶክተር ይገረሙ አስፋው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ ህፃኗ የተወለደችው ልጅ መውለድ ፈልገው ለበርካታ ዓመታት ሳይሳካላቸው የቀሩት ወይዘሮ ጸንሰው እንዲወልዱ በሐኪሞች በተደረገላቸው ልዩ ዕርዳታ ነው። ዶክተር ይገረሙ እንዳሉት የህጻኗ ወላጅ እናት ከማህጸናቸው የተወሰደ ዕንቁላል ከባለቤታቸው ከተወሰደ የዘር ፈሳሽ ጋር በቤተሙከራ በማገናኘት እንዲጸንሱ ከተደገረ በኋላ ጽንሱ የዘጠኝ ወር ዕድገቱን በተፈጥሯዊ መንገድ በማህፀናቸው ውስጥ አጠናቆ እንዲወለድ ተደርጓል። በጣሊያናዊው ዶክተር ሊዎናርዶ ፎርሚጂሊ ሙያዊ ዕገዛ የተወለደችው ህፃን በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ በሐኪሞች ዕርዳታ የሴቷን ዕንቁላልና የወንዱን የዘር ፈሳሽ ከማህጸን ውጪ በማገናኘትና መልሶ ወደ ማህጸን በማስገባት ተፀንሳ የተወለደች ህፃን መሆኗን ገልፀው፤ በአሁኑ ወቅትም የእናቷን ጡት በመጥባት በመልካም ጤንነት እንደምትገኝ አስረድተዋል። በሴቷ ማህፀን የቱቦ መጥበብ ወይም በወንዱ ዘር ፈሳሽ ዓቅም ደካማ መሆን ምክንያት መፀነስ ላልቻሉ ጥንዶች የሚሰጠው በቤተሙከራ የታገዘ የማስፀነስ ህክምና በኢትዮጵያ የተጀመረው ባለፈው ዓመት መሆኑን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት 10 እናቶች በሐኪሞች ዕርዳታ ፀንሰው ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝም አስረድተዋል። በአገሪቱ በመስኩ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ባለመኖራቸው የሆስፒታሉ የማህፀን ሐኪሞች ልምዱን እየቀሰሙ መሆናቸውንም ዶክተር ይገረሙ ገልጸዋል። የህጻኗ እናት በበኩላቸው በተደረገላቸው የህክምና ዕርዳታ የሴት ልጅ እናት ለመሆን በመብቃታቸው እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፤ ልጅ ለመውለድ ጉጉትና ፍላጎቱ ኖራቸው የልጅ እናት ሳይሆኑ ለቀሩት ቤተሰቦች የምስራች ብለዋል። በመሆኑም ልጅ ለማግኘት እየፈለጉ መውለድ ያልቻሉ ቤተሰቦች ህክምናውን ቢሞክሩት ምኞታቸው ሊሳካላቸው እንደሚችል መክረዋል። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቤተሰብ ጤና እንክብካቤ መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ተስፋነሽ በላይ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ሆስፒታሉ በዚህ ረገድ ያስገኘው ውጤት የአገራችን የህክምና አገልግሎትን አንድ ዕርምጃ ወደፊት ያራመደ አበረታች ጅምር ነው ብለዋል። ሴት ልጅ በህይወት ዘመኗ ዕርግዝናን ማየት እንደምትፈልግና በማህበረሰባችን ልማድም ልጅ መወልድ የክብር መገለጫ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ተስፋነሽ፤ በቤተሙከራ የታገዘ የማስጸነስ ህክምና የስነ ተዋልዶ ጤና ፕሮግራም አካል በመሆኑ ሊበረታታ እንደሚገባ ተናግረዋል። ቀደም ሲል ይህንን የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ብዛት ያላቸው ባለትዳሮች ወደ ውጭ አገር ለመሄድ የገደዱ እንደነበር አስታውሰው፤ አገልግሎቱ በአገር ውስጥ መጀመር ወላዶች ከቤተሰቦቻቸው ሳይርቁ ለመውለድም ሆነ የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|