የአደረጃጀትና የሰው ሀይል ችግሮቹ የፍትህ ተቋማቱን አቅም ጠንካራ እንዳይሆን ማድረጋቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ መስከረም 25/1999/ዋኢማ/ በፍትህ ስርዕቱ አሰራር ላይ የሚታዩ የአደረጃጀትና የሰው ሀይል ችግሮች የፍትህ ተቋማቱ ዓቅም የተፈለገውን ያህል ጠንካራ እንዳይሆን አድርገውት መቆየታቸውን የፍትህ ሚኒስትሩ ገለጹ።

ሚኒስትሩ አቶ አሰፋ ከሲቶ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአራት ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ ላይ የሚነጋገረው የባለድርሻዎችና ተባባሪዎች ሰብሰባ ዛሬ ሲከፍቱ እንደገለጹት፤በፍትህ ተቋማቱ የታዩት የአደረጃጀትና የሰው ኃይል ችግሮች የፍትህ አካሉ የተጣለበትን የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የማስጠበቅና ለዘላቂ ሰላምና ዕድገት የማገዝ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዳይወጣ አድርገውታል።

በሀገር ውስጥና በውጭ ባለሙያዎች ተጠንቶ የቀረበው የስትራቴጅክ ጥናትም ብቃት ያለው የሰው ኃይል እጥረት፣የተቋማቱ በበቂ መሳሪያዎች አለመደራጀት፣ የአሰራር ዘዴዎችና ሥነ ሥርዓቶች ኋላ ቀር መሆን ፣ የፍትህ መረጃ ሥርዓት በአግባቡ ተደራጅቶ አለመገኘትና የቅንጅት ጉድለት ችግሮች እንዳሉ ማረጋገጡን ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

በጥናቱ የተረጋገጡት ችግሮችም የፍትህ አፈጻጸሙን ቀልጣፋና ፈጣን እንዳይሆን በማድረግ በአገሪቱ የንግድና ኢንቨስትመንት አካሄድ ላይ መሰናክል ከመፍጠራቸውም በላይ ህብረተሰቡ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ያለውን ዕምነት እንዲቀንስ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የአራት ዓመቱ ስትራቴጂክ ዕቅድ የማስፈጸም ዓቅም በመገንባት፣የወንጀል ፍትህ አሰተዳደርን በማሻሻል፣ በህግ ጥናትና ምርምር ፣ ለክልልና ለፌድራል መንግስት የህግ ማማከር ሥራ በመስራትና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ተግባራት መያዙን ሚኒስትሩ ጠቁመው፤ዕቅዱ ለአመራር አካላት፣ለመርማሪ ፖሊሶች፣ ለዓቃብያነ ህግ ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠትና አደረጃጀትን በማስተካከል የስራ አፈጻጸምን የማሳደግ ግቦች እንዳሉት አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ከአራት ዓመት በኋላ የአቃቤ ህግ በምርመራ መዝገቦች ላይ ውሳኔ የመስጠት አቅሙን አሁን ካለበት 58 በመቶ በዕጥፍ እንደሚያሳድገው የስትራቴጅክ ዕቅድ ሰነዱ አመልክቶ፤ በተለያዩ ምክንያቶች በዕቃቢ ህግ የሚዘጉ መዝገቦች ቁጥርን ደግሞ ከ56በመቶ ውደ 10 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ግብ መያዙን ጠቁመዋል።

እንዲሁም ተከሳሾችን የማስቀጣት ዓቅም አሁን ካለው የ13 በመቶ አፈጻጸም ወደ 70 በመቶ ከፍ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።

በስትራቴጂክ ዕቅድ ስብሰባው ላይ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ የባለድርሻዎችና የተባባሪዎች ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን በስብሰባው የተነሱ ነጥቦች ዕቅዱን ለማዳበር አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ከአስተባባሪዎቹ ገለፃ ለመረዳት መቻሉን ዋልታ ኢንፎርሜሸን ማዕከል ዘግቧል።