የፓራሊምፒክ ኮሚቴ ለመላው አፍሪካ ጨዋታዎችና ለቤጂንግ ኦሎምፒክ የሚቀርቡ ስፖርተኞችን በማሰልጠን ላይ ነው

አዲስ አበባ መስከረም 25/1999/ዋኢማ/ የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ በ2007 አልጀርስ ለሚካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎችና ለቤጂንግ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ 44 ስፖርተኞችን መልምሎ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፋንታሁን አልማው ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ ስፖርተኞቹ ባለፈው ዓመት በስምንት ክልሎች መካከል በተካሄደው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ውድድር ጥሩ ብቃት በማሳየት የተመረጡ ናቸው።

ስልጠናው በአትሌቲክስ፣ በጠረጴዛ ቴንስና በክብደት ማንሳት ላይ አተኩሮ እየተሰጠ መሆኑን የገለጹት አቶ ፋንታሁን፤ በተመለመሉት 44 ስፖርተኞች መካከል በሚደረግ የመጨረሻ የማጣሪያ ውድድር ያለፉት ብቻ ለውድድሩ እንደሚሄዱ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ናይጄሪያ በተደረገው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች 20 ስፖርተኞች ተካፍለው ውጤት ባይመጣም ከፍተኛ ልምድ የተቀሰመበት ውድድር እንደነበረ ኃላፊው አስታውሰው፤ የአሁኑ ዝግጅት የተሻለ ውጤት ይገኝበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር ለጽህፈት ቤታቸው የበጀት ድጐማ እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ፋንታሁን፤ የውጪና የአገር ውስጥ ድርጅቶችም የበኩላቸውን ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ህብረተሰቡም ሆነ አካል ጉደተኞች ራሳቸው አካል ጉዳተኛ በማንኛውም የልማት መስክና ስፖርታዊ እንቅስቃሴ መሳተፍና ውጤታማ መሆን እንደሚችል መገንዘብ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ኰሚቴ ድር ፋውንዴሽን ከተባለ የውጭ አገር ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር የቤጂንግ ፓራሊምፒክ ተሳትፎን በተመለከት በምስራቅ አፍሪካ ለሚገኙ የፓራሊምፒክ ኮሚቴ አገሮች የጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 2/1999 ድረስ የሚቆይ የአራት ቀናት የውይይትና የምክክር ሴሚናር አዲስ አበባ ላይ ማዘጋጀቱን ኃላፊው ገልፀዋል።

በአቴንስ ፖራሊምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ወንድ ስፖርተኛ በክብደት ማንሳት ውድድር ተሳትፎ እንደነበር የገለጹት ኃላፊው፤ ለቤጂንግ ኦሎምፒክ ብዛት ያላቸው ስፖርተኞችን ለማሳተፍ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የፖራሊምፒክ ስፖርት በየአራት ዓመቱ የኦሎምፒክ ውድድርን ተከትሎ የሚደረግ የአካል ጉዳተኞች ስፖርት መሆኑ ይታወቃል።