|
በዞኑ የዕጣን አምራች ማሕበራት የካፒታል መጠን 33 ሚሊየን ብር መድረሱ ተገለጸ |
አክሱም መስከረም 25/1999 /ዋኢማ/ በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን አምስት ወረዳዎች በዕጣን ማምረት የተሰማሩ 23 ማሕበራት ምርቶቻቸውን ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ካፒታላቸውን ወደ 33 ሚሊየን ብር ማሳደጋቸውን የየወረዳዎቹ እርሻና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤቶች አስታወቁ። የታህታይ አድያቦ ፣ የላዕላይ አድያቦ ፣ የአስገደ ጽምብላ ፣ የታሕታይ ቆራሮ እና የፀለምቲ ወረዳዎች እርሻና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤቶች ኃላፊዎች ሰሞኑን ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤በወረዳዎቹ በተቀናሽ የሰራዊት አባላት የተቋቋሙት 23 የዕጣን ማህበራት የተቀናጀ እንቅስቃሴ በማድረጋቸው የካፒታል አቅማቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። በዕጣን ማምረትና ማቅረብ ስራ ከሦስት ዓመት በፊት ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው ሲመሰረቱ የነበራቸው የካፒታል መጠን 4 ሚሊየን ብር ብቻ እንደነበር የገለፁት ኃላፊዎቹ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ120 ሺ ኩንታል በላይ ደረጃውን የጠበቀ ነጭና ጥቁር እጣን ወደ ማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ የካፒታል መጠናቸውን ወደ 33 ሚሊየን ብር ማሳደግ መቻላቸውን አስታውቀዋል። የማህበራቱ 1 ሺ 259 አባላት ከዘርፉ የሚያገኙትን ገቢ ለማሳደግ ያረጁ የዕጣን ዛፎችን ለመተካት በ60 ሺ ሄክታር መሬት ላይ በሦስት ዙር ከ300 ሺ በላይ የዕጣን ችግኞች መትከላቸውንም ኃላፊዎቹ ገልጸዋል። በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ምርታቸውን በዕጥፍ ለማሳደግ እቅድ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አስረድተዋል። ማሕበራቱ በየዓመቱ ከ6 ሺ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ጊዜያዊ የስራ ዕድል እየፈጠሩ መሆናቸውን ከኃላፊዎቹ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል። |
|
|
|
|