የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ለንግዱ ማህበረሰብ ስምንት ሚሊየን ዩሮ ብድር እንደሚሰጥ አስታወቀ

አዲስ አበባ መስከረም 25 /1999/ዋኢማ/ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የአገራችን የንግዱን ማህበረሰብ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማጠናከር የስምንት ሚሊየን ዩሮ ብድር እንደሚሰጥ አስታወቀ፡፡

በባንኩ የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ዳይሬክተር ሚስተር ካርሜሌ ኩኩዛ ትላንት ምሽት በአዲስ አበባ ንግድና የዘርፉ ማህበራት ምክር ቤት ስብሰባ አዳራሽ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ባካሄዱት ውይይት ባንኩ በንግድና በኢንቨስትመንት ለተሰማሩ ባለሃብቶችና ነጋዴዎች ብድር ይሰጣል፡፡

ባንኩ የሚሰጠው ብድር የግሉን የንግድና የኢንቨስትመንት ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሳደግ በልማቱ የአገር ውስጥና የውጪ ባለሃብቶችን አሳትፎ ለማጠናከር እንደሆነ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም የአገር ውስጥ የፋይናንስ ሴክተሩን አቅም በማጠናከር የንግዱን ማህበረሰብ ከባንኩ ጋር የሚኖራቸውን ትስስር በማጠናከር በአንድ ባንክ በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር እንደሆነም ሚስተር ካርሜሌ ኩኩዛ ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝደንት አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ በበኩላከቸው ባንኩ የሚሰጠው ብድር የፋይናንስ ችግር ያለባቸው ባለሃብቶችና የንግዱማህበረሰብ አባላት የኢንቨስትመንት ዘርፍን ለማጠናከር አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።

አፍሪካንናቀሪውን ዓለም የሚያገናኝ አንድ የአፍሪካ አለም አቀፍ የንግድ ማዕከል ለመገንባት በሚደረገው ጥረት በንግዱ ማህበረሰብና በአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ መካከል የሚደረግ ውይይት ለዚህ ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ተናግረዋል።

በግብርና፣ በአስመጪና ላኪነት፣ በአበባ ልማትና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ አንዳንድ ባለሃብቶችና ነጋዴዎች በበኩላቸው በኢንቨስትመንት ለመስማራት በቂ እውቀትና የሥራ ልምድ ቢኖራቸው በገንዘብ ዕጦት የሚፈልገውን ሥራ መስራት እንዳልቻሉ ገልፀዋል፡፡

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በ79 የአፍሪካ የካሪቢያንና የፓስፊክ ሃገራት ለ600 ሚሊየን ህዝብ ብድር በመስጠት እያገለገለ የሚገኝ ባንክ መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።