|
የዓለም ማህበረሰብ በሶማሊያ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ካልገባ በአህጉሩ ከፍተኛ ትርምስ ሊፈጠር እንደሚችል ተገለጸ |
አዲስ አበባ መስከረም 25/1999/ዋኢማ/ የዓለም ማህበረሰብ በሶማሊያ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ካልገባ በእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት ጥላ ስር ተከልሎ የሚገኘው አሸባሪ ኃይል መስፋፋት ለቀጣናውና ለአህጉሩ ሠላም መናጋት ከፍተኛ ጠንቅ እንደሚሆን በሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ጥናት ያካሄዱ አንድ ምሁር ገለጹ። በቅርቡ ሞቃዲሾን ጎብኝተው የተመለሱትና በህብረቱ እንቅስቃሴ ላይ ጥናት ያካሄዱት ዶክተር ማት ብራይደን የኢስት አፍሪካን ግሩፕ ትናንት በሸራተን ሆቴል ባዘጋጀው በሶማሊያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚነጋገር መድረክ ላይ እንደገለጹት፤ የህብረቱ መሪዎች ይዞታቸውን ወደ ሁሉም የሶማሊያ ማዕዝኖች ለመስፋፋት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። የእስላማዊ ፍርድ ቤቱ ህብረት የሚመሩትን ሆነ በህብረቱ ጥላ ስር ላሉት ኃይሎች የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማትና በሶማሊያ ያለውን ቀውስ እንዲባባስ የሚያደርጉ አካላት መበራከት ለህብረቱ ያልተገታ የመስፋፋት ፍላጎት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑ ዶክተር ማት ብራይደን ተናግረዋል። ይህም ሁኔታ በህብረቱ ጥላ ሰር ተከልለው ለሚገኙት እንደ አልኢትሐድ የመሳሰሉ አክራሪ ኃይሎች የአሸባሪነት ዓላማቸውን ለማሳካት እንደሚረዳቸው አስረድተዋል። የእነዚህ ኃይሎች መስፋፋት ሶማሊያን ማለቂያ ወደሌለው ቀውስ ከመክተት አልፎ በአካባቢው አገራት ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የሚያደርግና ቀጣናውን የሚያውክ በመሆኑ ጉዳዩ የሶማሊያውያን የውስጥ ችግር ነውና ለነሱ መተው አለበት ተብሎ መታለፍ እንደማይገባው ዶክተር ብራይደን አስገንዝበዋል። በመሆኑም የዓለም ማህበረሰብ ለጉዳዩ ተገቢ ትኩረት በመስጠት ዲፕሎማሲያዊም ሆነ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል። የዓለም ህብረተሰብ በእነዚህ ኃይሎች የኢኮኖሚ ማዕቀብና ጫና በመፍጠር የሽግግር መንግስቱን ጨምሮ ሁሉም የሱማሌ ኃይሎች ለውይይት የሚቀርቡበትና ወደ አካባቢው የሰላም አስከባሪ ሃይል የሚሰማራበት ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ከዚህ በተጨማሪም በሶማሊያ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በህዝብ የተመረጠውን የሶማሌ ላንድ አስተዳደር ላይ ኢንቨስት በማድረግ የአክራሪዎቹን ጫና ተቋቁሞ ለአካባቢው የዴሞክራሲ ሞዴል ሆኖ የሚንቀሳቀስበት ዕድል መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል። በሶማሊያ ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸው የአፍሪካ ህብረትም ሆነ የዓረብ ሊግ መንግስታት ለአካባቢው ሰላም መስፈን ጠንክረው ካልሰሩ በአካባቢው የሚፈጠረው ቀውስ ቀላል እንደማይሆንም ዶክተር ብራይደን ገልጸዋል። የዓለም ማህበረሰብ እንዲህ ዓይነት የአንድነትና የጣልቃ ገብነት ዕርምጃ ካልወሰደ በሶማሊያም ሆነ በቀጣናው በቀላሉ መመለስ የማይቻል ጥፋት ይከሰታል የሚል ስጋት እንዳላቸው ምሁሩ ተናግረዋል። የቀድሞው "የኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ" ከፍተኛ ተመራማሪ የነበሩት ዶክተር ማት ብራይደን በሶማሊያ ጉዳይ ላይ ተከታታይ ጥናት በማካሄድ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በርካታ ጽሁፎች ያቀረቡ ምሁር ናቸው። ለግማሽ ቀን በተዘጋጀው መድረክ ላይ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ምሁራንና የፖለቲካ ሰዎች መገኘታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜኝን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|