በጋምቤላ ክልል ፈቃድ ከወሰዱት26 ባለሀብቶች መካከል ዘጠኙ ማምረት መጀመራቸው ተገለፀ

ጋምቤላ መስከረም 25/1999/ዋኢማ/በጋምቤላ ክልል 100 ሚሊየን ብር ካፒታል አስመዝግበው ፈቃድ ከወሰዱ 26 ባለሃብቶች መካከል ዘጠኙ ማምረት መጀመራቸውን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ገለፀ፡፡

በኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነትና የጽሁፍ ህትመትና ዝግጅት ባለሙያ አቶ ደረጀ ፍሰሃ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤በግብርና፣በአግሮ ኢንዱስትሪ፣በሆቴልና በሪል ስቴት መኖሪያ ቤት ግንባታ ዘርፍ ከሁለት ዓመት በፊት ፈቃድ ከወሰዱት 26 ባለሀብቶች መካከል በግብርናና ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ዘጠኝ ባለሀብቶች ማምረት ጀምረዋል።

ቀሪዎቹ ባለሀብቶች በግንባታ ላይ እንደሚገኙና በቅርቡ ወደ ማምረት እንደሚገቡ ጠቁመው፤በተለይ በግብርናው ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች በቡና፣ ጥጥ፣ ሻይ ቅጠልና በሌሎች ቅመማ ቅመም ልማት ዘርፍ ላይ እንደሚያተኩሩ ተናግረዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱት ባለሃብቶች ሙሉ ለሙሉ ማምረት ሲጀምሩ ከአምስት ሺ ለሚበልጡ ወገኖች የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩ አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ የባለሃብቶችን ቁጥር ለመጨመር በአሁኑ ወቅት ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ምቹ የሆነ የመንገድ፣ የመብራት፣ የስራ የውሃ አገልግሎት የሟሟላት ተግባር በመከናወን ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።