ለብዝሀ ሕይወት ጥበቃ ኅብረተሰቡን ማሳተፍ እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ግርማ አሳሰቡ

አዲስ አበባ መስከረም 24/1999 - የሀገሪቱን የብዝሀ ሕይወት ሀብት ለመጠበቅ እየተደረገ ባለው ጥረት ኅብረተሰቡን ማሳተፍ እንደ ሚገባ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ አሳሰቡ፡፡ትናንት የብዝሀ ሕይወት ጥበቃና ድህነት ቅነሳ በሚል መርህ በግዮን ሆቴል የተጀመረውን ዓውደጥናት በንግግር የከፈቱት ፕሬዚዳንት ግርማ እንደገለጹት፤ መንግሥት ብዝሀ ሕይወትን ለመጠበቅ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን ያከናወነ ቢሆንም የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ኅብረተሰቡን ማሳተፍ ይገባል፡፡

አገሪቱ በዓለም ላይ የብዝሀ ሕይወት ሀብት በብዛት ካላቸው አገሮች መካከል እንደምትመደብ የገለጹት ፕሬዚዳንት ግርማ፤ ብዝሀ ሕይወት ለሰው ልጅ የሚኖረው ጠቀሜታ የጐላ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ አደጋ እየገጠመው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡የሕዝብ ብዛት መጨመርን ተከትሎ ነዋሪው ወደ ጥብቅ የብዝሀ ሕይወት አካባቢዎች ዘልቆ በመግባት ደን በመመንጠርና ለእርሻ በማዋል ለብዝሀ ሕይወት ሀብቱ መመናመን የራሱን ተጽዕኖ እንደ ሚያሳድር አመልክተዋል፡፡

የብዝሀ ሕይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ግርማ ባልቻ በበኩላቸው፤ አገሪቱ ከደን፣ ከመሬትና ከእንስሳት ጥበቃ ጋር የተያያዙ ሕጐችን ማውጣቷንና፣ የአካባቢና የብዝሀ ሕይወት ፖሊሲ እንዲሁም የኃይል ፖሊሲ አውጥታ ተግባራዊ ማድረጓን አመልክተዋል፡፡ ብዝሀ ሕይወትን ለመጠበቅ የሚጠበቅባትን ሁሉ ለማድረግ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መፈረሟንም ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ አዲስ የአካባቢ ጥበቃ አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋቷንም አመልክተዋል፡፡የኢትዮጵያ የቡና ደን መድረክ የቦርድ ሊቀመንበር በበኩላቸው የሕዝቡን ኑሮ በማሻሻል ተፈጥሮን መጠበቅ እንደ ሚያስፈልግ ጠቁመው፤ በተፈጥሮ ጥበቃው ሥራ ሕዝብን ማሳተፍ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ አገሪቱ ካላት የብዝሀ ሕይወት ሀብት አንፃር ተጠቃሚ አለመሆኗን ጠቁመው፤ መድረኩ ፖሊሲ አውጭዎችና፣ ኤክስፐርቶችን የሚመለከታቸውን ክፍሎች በተቀናጀ መልኩ በአንድ ላይ በማወያየት ወጥ የሆነ አቅጣጫ ለመቀየስ እንዲቻል ዓውደጥናቱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡