|
አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለናይጄሪያው ፕሬዚዳንት አቀረቡ |
| አዲስ አበባ መስከረም 24/1999
- በናይጄሪያ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርና ልዩ መልእክተኛ ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ የሹመት ደብዳቤአቸውን ለናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ሰሞኑን ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ፕሬዚዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ የሹመት ደብዳቤውን በጽሕፈት ቤታቸው በተቀበሉበት ወቅት የኢትዮጵያና የናይጄሪያ ግንኙነት ከናይጀሪያ ነፃነት በፊት የነበረና ተጠናክሮ በመቀጠል ላይ የሚገኝ መሆኑን መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡ ናይጄሪያ በቅኝ አገዛዝ በነበረችበት ወቅት ኢትዮጵያ ለሀገሪቱ የነፃነት ታጋዮች ያልተቆጠበ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን ፕሬዚዳንቱ አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ሀገሮች በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ለጋራ ጥቅም በጋራ እየሠሩ እንደሆነና በተለያዩ የአፍሪካና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ጠንካራ ትብብር እንዳላቸው መግለጻቸው ተመልክቷል፡፡ አምባሳደር ሱሌይማን በበኩላቸው የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት በኢኮኖሚው መስክ ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ የጠቆሙ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል ለናይጄሪያ ባለሀብቶች መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በናይጄሪያ ገበያ በጣም ተፈላጊ የሆኑ ምርቶች ያሏት ቢሆንም በናይጄሪያ መንግሥት ከውጭ እንዳ ይገቡ የተከለከሉ ምርቶች በመኖራቸው የንግድ ግንኙነቱ የሚፈለገውን ያህል አለማደጉን አምባሳደሩ አመልክተዋል፡፡በዚሁ ወቅት ፕሬዚዳንት ኦባሳንጆ በሰጡት ምላሽ፤ ወደ ናይጄሪያ ከውጭ እንዳይገቡ ከታገዱት ምርቶች ውስጥ ኢትዮጵያ ከአሁን ጀምሮ ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን ለናይጄሪያ ገበያ እንድታቀርብ ፈቅደዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በያዝነው የኢትዮጵያ ዓመት ኢትዮጵያን የሚጎበኙ መሆኑን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ኤምባሲ ከናይጄሪያ በላከው መግለጫ መግለጹን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመግለጫው አብራርቷል። ኢዜአ |
|
|
|
|